የሩስያ ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከበረ

1052

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ):-  የሩስያ ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከበረ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ እና  በኢትዮጵያ የሩስያ ፌደሬሽን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርክሂን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ የቋንቋ ቀን ከሰው ልጆች ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሰብዓዊነትና ሉዓላዊነት ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ቋንቋ የሆነው የሩስያ ቋንቋ ቀን በመላው ዓለም ባሉ የመንግስታቱ ድርጅት ቢሮዎች እንደሚከበርም ገልጸዋል፡፡

የሩስያ ቋንቋ ቀን የሩስያ ዘመናዊ ሥነ-ጽሁፍ አባት ተብሎ ከሚወደሰውና አፍሪካዊ ማንነት ከሚጋራው ዕውቁ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ልደት ጋር በማስተሳሰር የሚከበር ቀን መሆኑም ገልፀዋል።

ከ350 ሚሊየን በላይ ተናጋሪዎች ያሉት ሩስያኛ ቋንቋ በተለይም በማዕከላዊና ምስራቅ አውሮፓ ቀጣና በስፋት እንደሚነገር ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአሌክሳንደር ፑሽኪን ክፍል መደራጀቱንና በቋንቋ ማዕከሉ የሩስያ ቋንቋ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሩስያ ቋንቋ የሩስያዊያንን ሥልጣኔ፣ ባህልና ሥነ-ጽሁፍን ያቀፈ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ ለብዝሃ ቋንቋ ዕድገት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በቀጣይም የሩስያ ቋንቋ ለመማር ፍላጎት ያላቸው ሰራተኞች ሁሉ ለማስተማር በአዲስ አበባ ከሚገኘው የሩስያ ሳይንስና ቋንቋ ማዕከል ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርክሂን፤ ዕለቱ ብዝሃ ቋንቋና ብዝሃ ባህልን ለማስፋፋት እንደሚከበር ገልጸው፤ የቋንቋ ቀን ሲከበርም ከሰው ልጆች ማንነት፣ ሥልጣኔዎችና ቅርሶች ዐውድ አንፃር የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካላት ቋንቋን ፖለቲካዊ መልክ የማስያዝ አካሄዶች መኖራቸውን ጠቅሰው ሩስያኛ ቋንቋም በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ችግሮች የገጠሙት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቀኑን እንዲከበር በማድረጉ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የሩስያ ቋንቋና ዕውቀትን ለኢትዮጵያዊያንና በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች ለማስፋፋትም በአዲስ አበባ የፑሽኪን የሳይንስና ባህል ማዕከል እየተሰራ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአውሮፓውያኑ 2010 የሩሲያ ቋንቋ በየዓመቱ እንዲከበር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኮሚሽኑ አዳራሽ በየዓመቱ ይከበራል።   

የመንግሥታቱ ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ቀኑን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ቀጥሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም