አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የኮሪያ ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት የተፈረመበት 70ኛ አመት መታሰቢያ ስነ-ስርዓት ላይ ተካፈሉ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የኮሪያ ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት የተፈረመበት 70ኛ አመት መታሰቢያ ስነ-ስርዓት ላይ ተካፈሉ
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ):-በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የኮሪያ ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት የተፈረመበት 70ኛ አመት መታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ ተሳትፈዋል።
የመታሰቢያ ስነ ስርዓቱ የተካሄደው በጋንግዎን ግዛት በምትገኘው ቹንቼዎን ከተማ ሲሆን በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት አምባሳደሮችና ወታደራዊ አታሼዎች በመርሐ-ግብሩ ላይ መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጋንግዎን ግዛት አስተዳዳሪ ኪም ጂን-ቴ በስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኮሪያ ሪፐብሊክ ሰላም እውን የሆነውና የተረጋገጠው የኮሪያ ወታደሮች እና ከ22 አገራት የተውጣጡ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወታደሮች በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል።
በጦርነቱ 40 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮች ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውሰዋል።
“የጋንግዎን ግዛት ነዋሪዎች ቀደምት አባቶቻቸው ለአገራቸው የነበራቸውን ጀግንነት የተሞለባት ፍቅር እና ታማኝነት ሁሌም እያወሱት ይኖራሉ” ብለዋል የግዛቷ አስተዳዳሪ።
በደም እና በላብ የተገኙትን እንደ ነጻነት፣ሰብዓዊ መብቶች እና ሰላም ያሉ ዓለም አቀፍ እሴቶችን ለመጠበቅ የመሪነት ሚናውን ለመውሰድ እንደሚተጉም ገልጸዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም ስምምነቱ የተፈረመው እ.አ.አ ሐምሌ 27/1953 ነበር፤ ከስምምነቱ በተጨማሪ የጦር ምርኮኞች ልውውጥም ተደርጓል።