በሲዳማ ክልል ማረሚያ ቤቶች  ያለው የታራሚዎች  መልካም አያያዝ  ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ቋሚ ኮሚቴው

ሀዋሳ  ግንቦት 28 /2015 (ኢዜአ)፡-  በሲዳማ ክልል ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች   አያያዝ ዙሪያ ያለውን መልካም  ሁኔታ  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ የሀዋሳ ማዕከላዊ ማረሚያ ተቋምንና በሀዋሳ ከተማ የመሀል ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያን ተመልክቷል።

በዚህ ወቅት  የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ ወይዘሮ ዘሀራ ቢፍቱ፤  በማረሚያ የሚገኙ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸውና አስፈላጊ መሰረታዊ አቅርቦቶች እንደተሟሉላቸው ከምልከታቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ለታራሚዎቹ የምግብ፣ የህክምና አገልግሎትና ትምህርት ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል እየተማሩ እንደሚገኙ፤ በማረሚያው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ወስዶ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻለ ታራሚ እንዳለ ማወቅ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ መስኮች በማህበር ተደራጅተው ስራ እንዲሰሩና ገቢ አግኝተው ከራሳቸው ባለፈ ቤተሰቦቻቸውን መደጎም የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩንም መረዳት እንደቻሉ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በማረሚያው ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም ሁኔታ ለሌሎችም ተሞክሮ መሆን የሚችል እንደሆነ ገልጸው፤ ከማደሪያ ቤቶች አንጻር ጥበት መኖሩ እንደክፍተት የታየ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በማረሚያ ቤቱ ባየነው ነገር ተደስተናል፤ በቀጠሮ የሚመላለስ እንደሌለ ተረድተናል ያሉት ቡድን መሪዋ፤ ከይቅርታና ምህረት  ጋር ተያይዞ ያለው ቅሬታ ለመፍታት ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮንታሞ ቡርቃ በበኩላቸው፤ ክልሉ ከተመሰረተ ሶስት ዓመት እድሜ እንዳለውና ከዕድሜው አንጻር ያሉት ሁለት ማረሚያ ቤቶች ብቻ በመሆናቸው የታራሚዎች ቁጥርና ማደሪያ ክፍል አለመጣጣም እንደሚታይ አስረድተዋል። 

በማረሚያ ቤቱ ከለውጡ በፊት በነበረው ሁኔታ በታራሚዎች ላይ በኮሚሽኑ ፖሊሶች ይደርስ የነበረ ሰብዓዊ መብት ጥሰትን ከታራሚዎችና ከፖሊስ ሀይሉ ጋር በመነጋገር ጥፋቶችን በመለየት እርምጃ በመወሰዱ  ማስቀረት ተችላል ብለዋል።

በማረሚያ ቤቱ ከሚገኙ የህግ ታራሚዎች ውስጥ አስተያየቱን የሰጠው የታራሚዎች ኮሚቴ ጸሀፊ አዳነ ለማ እንዳለው፤  ከለውጡ በፊት በታራሚዎች ላይ ይደርስ የነበረው በደልና የመብት ጥሰት ቀርቷል።

አሁን ሁሉም ነገር ተለውጦ ታራሚው መብቱ ተከብሮለት በጥሩ ሁኔታ የእርማት ጊዜውን እንደሚያጠናቅቅም ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም