በደቡብ ክልል የኮሌራ በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ዲላ ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ክልል የሚታየውን የኮሌራ በሽታ ስርጭትና ተጋላጭነት ለመቀነስ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በበሽታው ስርጭት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ አካሂዷል።

በቢሮው የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወንድዬ በሽር በመደረኩ እንዳሉት  የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ተግባር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። 

በተለይም በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች የታየውን ስርጭት ለመግታት ቢሮው ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰብ ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት አምስት ቀናት በተካሄደ የክትባት ዘመቻ 178 ሺህ በላይ ዜጎች መከተባቸውንና ሌሎች የጤና አገልግሎት ተደራሽ እየተደረጉ መሆናቸውን ከፍተኛ ባለሙያው አስረድተዋል።

በክልሉ የበሽታው ምልክቶች ከታየባቸው 2 ሺህ 511 ዜጎች ውስጥ ከ93 በመቶ የሚልቁት የሕክምና አገልግሎት አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት ለመግታት የህብረተሰቡን የንጽህና አጠባበቅ ግንዛቤ ለማሳደግ የጋራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ወንድዬ አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ህብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና እንዲጠብቅ በማስተማር ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

''የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተቀናጀ ምላሽ ያስፈልጋል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ቀዲሬላ አህመድ ናቸው።


 

በተለይ ለህብረተሰቡ የንጹህ ውሃ ተደራሽነትን ከማሳደግ ባለፈ፤ በሽታውን በዘላቂነት እንዲከላከል ግንዛቤውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ለወረርሽኙ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የጥንቃቄ ሥራዎች  እንዲከናወኑም ጠቁመዋል።

በተለይ የተበከለ ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት ስለሚሆኑ ህብረተሰቡ ለግልና አካባቢ ጽዳት አጠባበቅ ትኩረት እንዲሰጥ በተቀናጀ መንገድ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ መምህር አስናቀ እንድሪያስ መድረኩ በበሽታው ስርጭት ዙሪያ ወቅታዊ መረጃ የሰጠ፣ በሽታውን ስርጭት ለመግታት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሚረዳው መልኩ በማስተማር ከበሽታው እንዲጠበቁ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም