በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሀብት ብክነትን ለመቀነስና የአሰራር ሥርዓት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው-  የዩኒቨርሲቲው  ከፍተኛ አመራሮች

130

 

ዲላ ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ) --የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሃብት ብክነትንና ለመቀነስና የአሰራር ሥርዓትን በማሻሻል ብልሽቶችን ለማረም እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው  ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ዩኒቨርሲቲውን በቀጣይ የራስ ገዝ ለማድረግ ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍቃዱ ወልደማሪያም እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በኦዲት ግኝት የተለዩና ሌሎች ችግሮችን ለማስተካከል እየተሰራ ነው።

በዚህም ብልሽቶችን በማረም አመራሩን ሪፎርም ከማድረግና ተጠያቂነትን ከማስፈን ጀምሮ የአሰራር ሥርዓቱን እስከ ማሻሻል የዘለቁ ተግባራት እየተካሄዱ ነው ብለዋል።

በሁሉም የትምህርት ክፍሎች የሚታዩ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን በጥናት በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም  ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በተለይም ብልሽቶች ገነው በወጡባቸው በግንባታ ፕሮጀክቶችና በተማሪዎች አገልግሎት የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የሕግ ተጠያቂነትን የማረጋገጥና የተመዘበረ ሃብት የማስመለስ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለተቋም ግንባታ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በሰው ሃብት አስተዳደርና ልማት ላይ የታዩ ብልሽቶች እስኪታረሙ በጊዜያዊነት ቅጥርና ምደባ እንዲቆም መወሰኑን አስታውቀዋል።
 

በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ብልሽቶችን በማረም ለኦዲት ግኝት ምላሽ ከመስጠት ባለፈም፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ለማድረግ የጸደቀውን ዓዋጅ ለመተግበር አቅም እንደፈጠረ አመላክተዋል።

በተለይ የሃብት ብክነትን ለመቀነስና የአሰራር ሥርዓት በማሻሻል ክፍተቶችን በዘላቂነት ለማረም እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ፍቃዱ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተከናወኑት የዳታ ማዕከል፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶችና መሰል የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ የግዥ ብቻ ሳይሆን፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር እንዳለባቸው ያነሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ዳራሪ ሰናይ ናቸው።

የዘገዩ፣ የግንባታ ውልና የመረካከቢያ ሰነድ የሌላቸው በሚል ፕሮጀክቶችን በስድስት ዘርፎች በመከፋፈል በተቋም አቅምና በባለድርሻ አካላት የማጥራት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
 

በዚህም የመንግሥትን የግዥና ንብረት አስተዳደር ዓዋጅን ባልተከተሉና ችግር ያለባቸው የግንባታና አማካሪዎች ጋር የነበሩ ውሎች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ መደረጉን አስታውቀዋል።

በተለይ የተጋነኑ የግዥ ውሎችን በመሰረዝና አማካሪ ድርጅቶችን በማገድ የመንግሥትና የዩኒቨርሲቲውን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ለህጋዊ ተቋራጮች መተላለፋቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

በዚህም የዘገዩ የመምህራን ቤቶች ግንባታና መለስተኛ ስታዲዬም ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲውን አሰራር ችግሮች በማረም ቁመናውን ከማስተካከል በላይ የራስ ገዝ አስተዳደርን እውን የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በተለይ የፋይናንስ ነጻነትን ለማረጋገጥ ዓዋጁን መሠረት ያደረጉ የገቢ አቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ኢንጂነር ዳራሪ አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው በኦዲት ግኝት የተለየ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብና ለሌሎች ብልሹ አሰራሮች እንዲስተካከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም