በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል ተገኘ

174

አርባ ምንጭ ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል መገኘቱን አንድ ዓለም አቀፍ የተመራማሪ ቡድን አስታወቀ።

12 አባላትን የያዘው ዓለም አቀፍ የቅሪተ አካል ተመራማሪ ቡድን በባሌ ተራሮች ስር ባካሄደው ተከታታይ አምስት ዓመታትን በፈጀ ጥናት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዕድሜ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል ማግኘቱን ገልጿል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት በተገኘው ቅሪተ አካልና የጥናት ሂደቱን የተመለከተ ለተለያዩ አካላት ገለጻ ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በእሥራኤል አገር ሂብሪው ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም ቅሪተ አካሉን ያገኘው ተመራማሪዎች ቡድን አስተባባሪ ዶክተር ተገኑ ጎሳ ጥናቱንና ግኝቱን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ቡድኑ በባሌ ሰንሰለታማ ተራሮች ግርጌ ስር ባደረገው ጥናት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዕድሜ ያለው የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል መገኘቱን አረጋግጠዋል።

ቅሪተ አካሉ የተገኘው በፈረንጆች አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም ሲሆን የግኝቱ ትክክለኝነት የበለጠ ለማጠናከር ተጓዳኝ የጥናት ሂደቶች ሲከናወኑ ቆይተው ግኝቱ ይፋ ሆኗል ብለዋል።

በጥናቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው የቀይ ቀበሮ ግማሽ የመንጋጋው ክፍል የተገኘ መሆኑን አረጋግጠው እስከ ቅርብ ጊዜ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህም ይበልጥ ጥናቱ ጎልብቶ የተረጋገጠ መረጃ ለዓለም ለማበርከት ሲባል መሆኑን ገልጸው ሂደቶቹ መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ዛሬ ይፋ መደረጉን ነው የተናገሩት።

በዚሁም ቅሪተ አካሉ አሁን ካሉ የቀይ ቀበሮዎችና መሰል እንስሳት ጋር ያለው አንድነትና ልዩነት እንዲሁም የዕድሜና ሌሎች ጥናቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

ቀይ ቀበሮዎቹ በሀገራችን በሰሜንና ባሌ ተራሮች አካባቢ የሚገኙ ሲሆን ህብረተሰቡ ለግጦሽና ለእርሻ መሬት ፍለጋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብሎም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ የዱር አራዊቱ በአሁኑ ሰዓት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፈሰር በሃይሉ መርደኪዮስ፣ ግኝቱ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሌሎች ዓለማት የማይገኙ የዱር እንስሳት ባለቤት መሆኗን ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም የሚሆን ማስረጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የመርሃ ግብሩ ዓላማም በመጥፋት ላይ ያለውና ብቸኛ የሆነው ቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል መገኘቱን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ዝሪያውን ከመጥፋት መታደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ይህ ግኝት በኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች አስተባባሪነት የተገኘ መሆኑን ያስታወሱት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሰይድ አህመድ ናቸው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት ለቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው ለዝሪያቸው አስፈላጊው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ ተቋም በጥናት የተደገፈ መረጃ በመስጠት የማንቃትና ሌሎች ሃላፊነቶች እየተወጣ መሆኑንም አብራርተዋል።

ጥናቱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም ተከታታይ ዓመታት የፈጀ ሲሆን በዚሁም ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጨምሮ 10 የተለያዩ ሀገራት ተመራማሪዎች በአጠቃላይ 12 ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች መሳተፋቸው ተመላክቷል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም