በሶማሌ ክልል ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

243

ጅግጅጋ ግንቦት 28 / 2015(ኢዜአ)፡-  በሶማሌ ክልል  የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ  ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ካራማራ ተራራ ላይ ዛሬ ዕለቱን በተመለከተ ውይይትና በችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተከብሯል። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ መንግስት   ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱላሂ  አደን  ዕለቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ እንደ ማህበረሰብ  አካባቢን መንከባከብና መጠበቅ ካልተቻለ   ለቀጣይ ትውልድ አስቸጋሪ መልካምድር እየተፈጠረ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል። 

ሰዎች በደኖች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት በሚፈጠረው በረሐማነት አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ በዝናብ እጥረት ለተደጋጋሚ ድርቅ እየተጋለጠ ነው ያሉት  አቶ አብዱላሂ፤ የክልሉ መንግስት ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ልዩ ትከረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የሶማሌ ክልል አካባቢ ጥበቃና የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሁየዲን አብዲ በበኩላቸው፤ ቢሮው  ከአካባቢ ጥበቃ ስራ ባሻገር በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ ሰፊ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። 

አለም አቀፉን የአካባቢ ጥበቃ ቀንን  በካራማራ ተራራ ላይ መከበሩም የተራራውን ብዝሐ ህይወትና ታሪካዊ ሥፍራነቱን ለመጠበቅ ያግዛልም ብለዋል። 


 

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና  ፕላስቲክ   አወጋገድ ላይ ትልቅ ክፍተት ያለበትና  የከተማ ብክለት እያስከተሉ  በመሆናቸው ለመከላከል ሁሉም ባለ ድርሻ አካል በቅንጅት መስራት እንዳለበት ያመለከቱት  ደግሞ የጅግጅጋ ከተማ  አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር  ዚያድ አህመድ ናቸው።  

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያም በጅግጅጋ ከተማ በደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ስራ ላይ የተሻለ  ውጤት ያስመዘገቡ ማህበራት እውቅና እና  ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። 

"የፕላስቲክ ብክለት ተፅዕኖን እንግታ " በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረው የአካባቢ ጥበቃ ቀን መርሃ ግብር ያዘጋጀው የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ነው።

በመርሃ  ግብሩ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም