የሰኔ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል--የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

236

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ)፣- የሁሉም ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከግንቦት 29 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በግንቦት ወር ሲሸጥ በነበረው ዋጋ እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

መንግሥት ባለፉት አመታት ከነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ሲደጉም ቆይቶ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉት ዜጎችን ያደረገ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚሁ አግባብ የነዳጅ ድጎማን ደረጃ በደረጃ ለማስቀረትና ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ጨምሮ ለዓመታት የተከማቹ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ሪፎርም በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመር እየተተገበረ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገው የታለመ ድጎማ አፈጻጸም በተጨማሪ በነዳጅ ግብይት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል ማንኛውም በነዳጅ ማደያዎች የሚደረግ ግብይት በዲጂታል ክፍያ ብቻ እንዲፈጸም በማድረግ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

ስለሆነም የታለመ የነዳጅ ድጎማንም ሆነ የነዳጅ ዲጂታል ግብይት ትግበራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሆኖ በነዳጅ ማደያዎች ይህንን ትግበራ በማደናቀፍ ህገ-ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላትን ላይ የተጠናከረ እርምጃ በየደረጃው የሚወሰድ መሆኑም አስታውቋል።

በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት መዋቅርና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ በታለመ ድጎማ ሰበብ የሚፈጸም ህገ-ወጥ ተግባርና በካሽ የሚፈጸም የነዳጅ ግብይት ላይ ተገቢውን ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ ሲል ሚኒስትር መስራ ቤቱ አሳስቧል፡፡

በዚሁ መሠረት፦

1. ቤንዚን ……………………………………… ብር 69.52 በሊትር

2. ነጭ ናፍጣ…………………………………… ብር 71.15 በሊትር

3. ኬሮሲን ……………………………………... ብር 71.15 በሊትር

4. የአውሮፕላን ነዳጅ …………………………. ብር 65.35 በሊትር

5. ቀላል ጥቁር ናፍጣ………………………….. ብር 57.97 በሊትር

6. ከባድ ጥቁር ናፍጣ………………………….. ብር 56.63 በሊትር

መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም