የጭሮ ከተማን ውብና ፅዱ ለማድረግ በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ

256

ጭሮ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)---በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የጭሮ ከተማን ውብና ፅዱ ለማድረግ በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ሊገነባ መሆኑን የከተማው አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማው ለ50ኛ ጊዜ የተከበረውን የአለም አካባቢ ቀን በማስመልከት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።


 

በዚሁ ጊዜ የተደራጀ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ መገንባትና ስርዓትን የተከተለ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲኖር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር፣ ጭሮ ከተማን ማራኪ ገፅታ ለማላበስ በየአካባቢው ቆሻሻ ስርዓት ባለው መልኩ እንዲወገድ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

''ጭሮን ውብ፣ ጽዱና ማራኪ ከተማ የማድረግ ግባችንን ለማሳካት የተደራጀ የቆሻሻ ማስወገጃ ሳይት ከማስገንባት በላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ መለወጥ ትልቁ ስራችን ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።

በተለይም በከተማው በስፋት ተጥሎ የሚገኘውን የፕላስቲክ መገልገያዎች አወጋገድን በተመለከተም ብዙ መሰራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የጭሮ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም በበኩላቸው ጭሮን ውብና ፅዱ ከተማ የማድረግ እቅዱን ለማሳካት በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ቆሻሻ ማስወገጃ ሊገነባ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ዘመናዊ የማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ገልጸው ለተደራጀ ቆሻሻ አወጋገድ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም ከቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሳምንታዊ የአካባቢ ፅዳት ዘመቻ እያካሄዱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ አወል ከተማዋን ፅዱና ውብ ለማድረግ ጽዳት ማከናወን ብቻ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ለቆሻሻ አወጋገዱም ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

ከተማዋ በተለይ በወንዞች ዳርቻ የፕላስቲክ ኮዳዎች በስፋት እየተከማቸ በመሆኑ ወንዞችን ጽዱ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እንደሚቻልም አንስተዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሙስጠፋ ሳሊ በበኩላቸው ተስማሚ አየር ያለበት ፅዱ አካባቢን እውን ለማድረግ ሁሉም በየራሱ መንደር ተጨባጭ ስራ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

ሁላችንም ቆሻሻን በዘፈቀደ ከመጣል መቆጠብና ይህን በተላለፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተጠያቂነት ማስፈን ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም