ቀጥታ፡

በኦማን የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሰማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደረገ


አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ በኦማን የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሰማራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ እና በኦማን የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች መካከል ውይይት ተደረገ።

በጉዳዩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦማን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል። 

ወደ ተለያዩ ሀገራት የሰለጠና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል በመላክ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ የተገለጸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነቶችን በመፈፀም እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል። 

ከኦማን የቪዛ፣ የህግ፣ የውጭ ጉዳይ እና ከሠራተኛ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኃላፊዎች ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን ጋር ተወያይተዋል።


 

የውይይቱ ዓላማ አዲስ ስምምነት በመፈፀም ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር እና ወደ ኦማን የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሰማራት መሆኑን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል። 


የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 77 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አረብኛ ቋንቋን ጨምሮ ሊሠሩ በሚችሉበት ሙያ ለማሰልጠን ዝግጁ መሆናቸውንም  አስታውቀዋል።


ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ባለሙያዎችን ለዓለም አቀፉ የሥራ ገበያ ለማቅረብ እየሠራች ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። 

ኦማን መብታቸውን አስጠብቃ የምታሠራቸው ሠራተኞችን እንደምትፈልግ እና ለዚህም የቀድሞውን ስምምነት ማደስ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ማዘጋጀታቸውን የኦማን የሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ገልፀዋል። 


ወደ ኦማን የሚላኩ ዜጎች መብታቸው እንዲጠበቅ ስለምንፈልግ ረቂቅ ሰነዱን የህግ ባለሙያዎች በጥልቀት ተመልክተው በኤምባሲዎች በኩል እንደሚፈጸም አቶ ንጉሱ መግለጻቸው በመረጃው ተመላክቷል። 


ከኦማን የመጡት የሥራ ኃላፊዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ያበለፀገውን የመረጃ ስርዓት በተመለከተ ገለፃ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም