ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትሕ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

129

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ) ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትሕ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በወጡ ሕጎችና ማሻሻያዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።

የፍትሕ ሚኒስቴር አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የወጡ የሕግና አሠራር ማሻሻያዎችን በሚመለከት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትሕ ቢሮ፣ የፍርድ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት፣ የጠበቆች እና መሰል ሕጎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው፤ ለውጡን ተከትሎ በፍትሕና ሌሎችም ተቋማት የማሻሻያ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም አዲስ የወጡ አዋጆችና ማሻሻያዎችን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአግባቡ መተግበር እንዲያስችለው የግንዛቤ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፍትሕ ተቋማት በለውጡ ዓመታት በወጡ አዋጆች ላይ ሙሉ መረዳት ኖሯቸው ክልሉን በመደበኛ ሕግ ማስተዳደር እንዲችሉ የግንዛቤ መድረኩ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ተዋንያን ጋር የሚደረገው ውይይት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሀዱሽ ተስፋ፤ መድረኩ በመንግሥት የተደረጉ የፍትሕ ማሻሻያዎችን በአግባቡ በመረዳት ተግባራዊ ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም