ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ በአፍሪካ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራ አስፈጻሚ በሚል ተመረጡ

 

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ በአፍሪካ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራ አስፈጻሚ በሚል ተመረጡ። 

የዓለም ባንክ ግሩፕ አባል የሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር(አይ ኤፍ ሲ) እና ‘ዢን አፍሪክ ሚዲያ ግሩፕ’ የ2023 የአፍሪካ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራ አስፈፃሚዎች ይፋ አድርገዋል።


በኮትዲቫር አቢጃን በተካሄደው የአፍሪካ ስራ አስፈጻሚዎች ፎረም  በአፍሪካ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራ አስፈፃሚ በመባል ከተመረጡት ውስጥ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ ይገኙበታል።


በፎረሙ ላይ የአገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ ከ1 ሺህ የሚበልጡ  ስራ አስፈጻሚዎች የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ ያላቸውን ልምድና እውቀት ለታዳሚያን አጋርተዋል።



በተያያዘ ዜና ባለሀብቱ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር(አይ ኤፍ ሲ) ጋር የ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነት ከተቋሙ የስራ  ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።


የብድር ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን ለሚያከናውኗቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች ለማገዝ እንደሚያስችል ተገልጿል።


አይ ኤፍ ሲ በደቡብ ሱዳን የግሉን ዘርፍ በፋይናንስ ሲደግፍ አቶ አይሸሽም የመጀመሪያው ሲሆኑ ገንዘቡ በደቡብ ሱዳን ለሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች ተጨማሪ አቅምና ጉልበት እንደሚፈጥር መገለጹ ለኢዜአ የተላከው መረጃ ያመለክታል። 


አቶ አይሸሽም ተካ ከቀን ሰራተኝነት 7 ብር ደሞዝ ተነስተው በጠንካራ የስራ ትጋት የግዙፍ ኩባንያ ባለቤት መሆን የቻሉ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ናቸው። 
 


ላለፉት 15 ዓመታት ኑሯቸውን በደቡብ ሱዳን ጁባ ያደረጉት እኚህ ባለሀብት የተለያዩ የንግድ ስራዎችን በማከናወን የሚታወቁ ሲሆን በውጭ ሀገር በኢትዮጵያዊ  የተቋቋመ ብቸኛ ቴሌኮም ተቋም መመስረት ችለዋል። 


ባለሀብቱ በደቡብ ሱዳን በሰላም፣ልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እ.አ.አ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግስት የክብር ዜግነት የተሰጣቸው ሲሆን ሌሎች ብዙ እውቅናና ሽልማቶችን አግኝተዋል። 


ባለሀብቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡብ ሱዳን እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ እያበረክቱ በሚገኘው ተሳትፎ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ቢውልደርስ የሽልማት ድርጅት መስከረም 2015 እውቅናና ሽልማት ማበርከቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም