በጎንደር ከተማ ወጣቶች ከወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችና ከእምቦጭ አረም ቁሶችን በማምረት የስራ እድል እየፈጠሩ ነው

273

ጎንደር ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችንና የእምቦጭ አረምን በግብአትነት ተጠቅመው የመገልገያ ቁሶችን አምርተው በመሸጥ ለገቢ ማግኛ ማዋላቸውን በስራ ፈጠራ የተሰማሩ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የዓለም አካባቢ ቀን "የፕላስቲክ ብክለትና መፍትሄዎች’’ በሚል መሪ ሐሳብ በጎንደር ከተማ በፓናል ውይይትና በዐውደ ርእይ ዛሬ ተከብሯል፡፡

የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ስራዎችን ሰርተው በዐውደ ርዕዩ ላይ የስራ ውጤታቸውን ያቀረቡ ወጣቶች እንዳሉት በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ወዳድቀው የሚጠፉ ቁሶች እምብዛም አይኖሩም።

 የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ወጣት ምስጋናው ጀንበሬ እንደገለጸው ከወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶች መጥረጊያና ገመዶችን በመስራት  በዐውደ ርእዩ ላይ ለእይታ አቅርቧል።

አምስት ሆነው የጀመሩት ስራ አሁን ላይ ለ15 ተጨማሪ ለስራ ፈላጊ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር በቀን 800 የወዳደቁ የውሃ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

በቀን እስከ 40 የፕላስቲክ መጥረጊያዎችን አምርተው ለገበያ አቅርበው በመሸጥ ራሳቸውንና በስራቸው የቀጠሯቸውን ግለሰቦች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ በማከል።

በዚህም የፕላስቲክ ተረፈ ምርትን ጥቅም ላይ በማዋል የከተማውን ጽዳትና ውበት ከመጠበቅ ባሻገር በግድቦችና ጎርፍ መፋሰሻ ቦዮች ላይ ይደርስ የነበረውን ብክለት ማስወገድ መቻላቸውን አስገንዝበዋል።

በጣና ሀይቅ ህልውና ላይ የአደጋ ስጋት ደቅኖ የቆየውን የእምቦጭ አረም አድርቀውና ፈጭተውም አካባቢውን በማይበክል መንገድ ለወረቀት ስራ እየተጠቀሙበት ያሉት ደግሞ እነ ወጣት ሰለሞን ብርሃኔ ናቸው፡፡

የእምቦጭ አረምና የተጣሉ ቆሻሻ ወረቀቶችን በጥሬ እቃነት በማዋል የእቃ መያዣ ዘንቢሎችን፣ የሰርግ የጥሪ ካርዶችና የፋይል ማቀፊያዎችን በመስራትና በመጠቀም ለ20 ሴት ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉም አስረድቷል፡፡ 

በቀን አምስት ኩንታል የእምቦጭ አረምን በጥሬ እቃነት መልሶ በመጠቀም የአካባቢን ብክለት እየታደጉ መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ወደፊትም ስራውን በፋብሪካ ደረጃ ለማስፋት እቅድ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡  

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ጽዳትና ውበት አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምስጋናው ጀንበሬ በበኩላቸው በከተማው በአራት ማህበራት የተደራጁ ከ200 በላይ ወጣቶች ቆሻሻን መልሰው ጥቅም ላይ እያዋሉ ይገኛሉ፡፡

የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችሉ የስራ ፈጠራ ለተሰማሩ ወጣቶችና ኢንተርፕራይዞች የሙያ ስልጠና ከማመቻት ጀምሮ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ባለፉት 10 ወራት ከ145ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻን በማስወገድ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጥረት መደረጉንም ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም