የፕላስቲክ ምርቶች ለአካባቢ ብክለት መንስዔነታቸው እየጨመረ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ የፕላስቲክ ምርቶች ለአካባቢ ብክለት መንስዔነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ለማስወገድ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር  ኤጀንሲ ጠየቀ፡፡

ባለሥልጣኑ የዓለም የአካባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ400 ሚሊየን ቶን ፕላስቲክ የሚመረት ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በኢትዮጵያም የፕላስቲክ ምርቶች ለአካባቢ ብክለት መንስዔ እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል።
 

ለአብነትም በየዓመቱ  ከ900 ሺህ ቶን በላይ አዳዲስ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለው ከ5 በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ዶክተር  እሸቱ ለማ  እንዳሉት፤ የፕላስቲክ ምርቶች   በከተማው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ እና በአካባቢ ብሎም በእንስሳት ላይ ጭምር አደጋ እያስከተለ ነው።

በከተማው ጥቅም ላይ እየዋሉ  ያሉ አብዛኛው የፕላስቲክ ምርቶች የአገልግሎት ዘመናቸው አጭር ጊዜ ወይም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ነው።

በዚህም ሳቢያ የቆሻሻ ምርት መጠን እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑ ኤጀንሲው ብክለቱን ለመቀነስ እየሰራ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡ በተለይ የፕላስቲክ ምርቶች አወጋገድ  ላይ እየተሰራ ያለውን ሥራ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን  ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ በበኩላቸው፤ ዜጎች እፅዋትን በመትከልና በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ለመቀነስ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ፣ ብክለትን መከላከል፣ ካርቦን ልቀትን መቀነስና  ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ማቃጠያዎች የሚላከውን የቆሻሻ መጠን መቀነስ  ይገባል ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ዓላማም የአካባቢ ብክለትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁሳቁሶችን በግለሰብ ደረጃ በአግባቡ በማስወገድና ወንዞችን ከብክለት መጠበቅ እንዲቻል ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን  ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም