የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል - ፕሬዝዳንቱ

179

ባህር ዳር ግንቦት 28/2015(ኢዜአ) የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  በ60 ዓመታት ጉዞው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያበረከተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የመዝጊያ ሥነ ሥርዓትና የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀንን አስመልክቶ በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር  ዛሬ አካሂዷል።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት  ስድስት አሥርት አመታት ለአገሪቷ የሰው ኃይል በማሰልጠን፣ በጥናትና ምርምርና ማሀበረሰብ አገልግሎት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ወደፊትም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ልዩነት የሚፈጥሩና የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ በማተኮር በአፍሪካ ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በምርምር የተደገፉ ተግባራት ከማከናወን ባለፈ፤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

መንግሥት ይፋ ያደረገውን የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ውጤታማ ለማድረግም አርሶ አደሩን በግብዓት የመደገፍ፣የማማከርና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግም በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከባለሃብቶች ጋር ተባብሮ በማስገንባት አሻራውን በማሳረፍ ላይ ነው ብለዋል።

ከፕሮጀክቶቹም የባህር ዳር አብርሆት ቤተ መጻህፍት፣ ልዩ ትምህርት ቤትና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደሚገኙበት ዶክተር ፍሬው አስታውቀዋል።

በቤዛዊት ተራራ የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብርም ዩኒቨርሲቲው ለሥነ-ህይወታዊ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው አረንጓዴ ልማት ለሰብል፣ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ ዓይነተኛ መፍትሄ መሆኑን አመልክተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ትውልድን በእውቀትና በአመለካከት ከመቅረጽ ባሻገር፤ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነውን  የአካባቢ ሥነ-ምህዳር በመጠበቅ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ከሚያስጠብቁ ሥራዎች መካከል ሥነ-ህይወታዊ ሥራዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መተግበር እንደሚኖርባቸው አስረድተው፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው አካታች የሆነ ሥነ-ህይወታዊ ሥራ በመስራት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይም በክልሉ አምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ፈጥኖ በመጀመሩ ሌላውን ህብረተሰብ የማነሳሳት ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፤ ቢሮውም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች  ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል ለአምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አመራሮች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም