በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ይበልጥ እንዲጠናከር የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ  

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ይበልጥ እንዲጠናከር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች " የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ እና አንዳንድ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች " በሚል ርዕስ ውይይት አድርገዋል፡፡ 
 

በመድረኩ የውይይት የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፌዴራሊዝም እና መልካም አስተዳደር ምሁሩ ዶክተር ዘመላክ አይተነው፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን አንስተው ይህም ለተጠናከረ መድብለ ፓርቲ ግንባታ ሕጋዊ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ አገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው እና  ሕገ-መንግስቱ ለቡድንና ግለሰብ መብቶች እውቅና መስጠቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለመገንባት በጎ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

ነገር ግን ጠንካራና የተደራጁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አለመኖራቸው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በሚፈለገው አግባብ እንዳይጎለብት አድርጓል ነው ያሉት ዶክተር ዘመላክ።

በመሆኑም የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ 
 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የቦርዱ አዋጅም ሆነ ሕገ-መንግስቱ የመድብለ ፓርቲ አካሄድን የሚፈቅድ ነው ብለዋል፡፡ 

በዚሁ መሰረት 21 አገራዊ እና 41 ክልላዊ በድምሩ 62 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ሰብሳቢው አክለው የመድብለ ፓርቲው ስርዓት ይበልጥ እንዲጎለበት ሁሉም ፓርቲዎች ለሕግ ተገዢ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ማጎልበት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ኃላፊነት አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡
 

የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር ዮሐንስ ተሰማ  አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተከናወኑ ስራዎች ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ትግበራ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።  

ለአብነትም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት የአመራርነት መዋቅር ውስጥ መካተታቸውን አንስተዋል።
 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በቀጣይ ለሚካሄደው አገራዊ የምክክር ሂደት መሳካት ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤትም በውይይቶቹ የሚነሱ ሃሳቦችን አደራጅተው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚሰጡ  ጠቁመዋል።

ዛሬ የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ በቀጣይም በሌሎች አጀንዳዎች የሚቀጥል መሆኑ ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም