ለዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር የሐጅ ስነ-ስርአት ተጓዦች (ሁጃጆች) ሽኝት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር የሐጅ ስነ-ስርአት ተጓዦች (ሁጃጆች) ሽኝት ተደረገ
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ ለዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር የሐጅ ስነ-ስርአት ተጓዦች (ሁጃጆች) በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሽኝት ተደረገ።
የ1 ሺህ 444ኛው የሐጅ ስነ-ስርአት ጉዞ በዛሬው እለት የተጀመረ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 387 ሁጃጆች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ሌሎች የመጅሊስ ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ ኃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ሽኝት አድርገዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በ18 ማዕከላት የሐጅና ዑምራ አገልግሎት በዲጂታል በታገዘ መልኩ ፈጣን አገልገሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱ የምዘገባ፣ የቪዛና መሰል አገልገሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ለዘንድሮው (የ1 ሺህ 444ኛው) የመጀመሪያ ዙር የሐጅ ተጓዦች (ሁጃጆች) ሽኝት መደረጉን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የሃጅ ጉዞም ከዛሬ ጀምሮ በቀጣዩ ወር የሚቀጥል መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያደረገ ላለው መልካም መስተንግዶ አድንቀዋል።
አየር መንገዱ ለሁጃጆች የሚሰጠውን ቀልጣፋና መልካም መስተንግዶ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።