በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላት ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦በአገር አቀፍ ደረጃ የሥራ ፈጠራ ክህሎትን ለማስፋት የሚያስችሉ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።  

"ብሩህ ኢትዮጵያ" የንግድ ሥራ ፈጠራ ኃሳብ ውድድር ተሳታፊዎች በቡራዩ ተሰጥዖ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት ሥልጠና መሰጠት ተጀመረ። 


 

ለ"ብሩህ ኢትዮጵያ" የንግድ ሥራ ፈጠራ ኃሳብ ውድድር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ 200 ተወዳዳሪዎች ተመልምለዋል። 

ተሳታፊዎቹ ከዛሬ ግንቦት 28/2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 17/2015 ዓ.ም የሚቆይ ሥልጠና በቡራዩ ተሰጥዖ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት መከታተል ጀምረዋል።  

ሥልጠናው በሥራ ፈጠራ፣ ኃሳብን ወደ ተግባር መቀየርና የንግድ አመሰራረትን በተመለከቱ ጉዳዮች  ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።  

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የመርኃ ግብሩ ዓላማ ማሰልጠን፣ መሸለምና ማብቃት ነው።


 

መርኃ ግብሩ ክትትልና ድጋፍን የሚያካትት መሆኑን ገልጸው የፈጠራ ኃሳቦች ወደ ተግባር ተቀይረው ሕዝብና አገር እንዲጠቅሙ ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ባሉ ውድድሮች ተወዳድረው በየደረጃው ያሉ አሸናፊዎች የፈጠሯቸው ኢንተርፕራይዞች ተስፋ ሰጭ ጅምሮችን እያሳዩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

ለሰባት ተከታታይ ጊዜያት በተካሄደው "ብሩህ ኢትዮጵያ" የንግድ ሥራ ፈጠራ ኃሳብ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ 381 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል። 

በአሁኑ ውድድር ለሚያሸንፉ 50 ባለ ኃሳቦች ለሥራ መነሻ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው የአምስት ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ውጤቶች እንዲበራከቱ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የቡራዩ ተሰጥዖ ማበልፀጊያም የዚሁ ሥራ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸው ማዕከሉ ወጣቶች አዳዲስ ኃሳብ እንዲያወጡ ተሰጥኦ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ታስቦ መገንባቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም መሰል ተቋማትን ወደ ክልሎች ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃሰን ሁሴን በበኩላቸው በማዕከሉ ቆይታ የሚያደርጉ ሥራ ፈጣሪዎች ሥልጠናውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተናግረዋል። 

 

 

 

 

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም