በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በ10 ሺህ ሜትር የሚወክሉ አትሌቶች የማጣሪያ ውድድር በስፔን ሊካሄድ ነው

348

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በ10 ሺህ ሜትር የሚወክሉ አትሌቶች ማጣሪያ ውድድሩን በስፔን ማላጋ ከተማ እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ። 

19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሀንጋሪ ቡዳፔስት በያዝነው ዓመት ነሐሴ ወር ውስጥ ይካሄዳል።

በዚህ ውድድር ተሳታፊ ከሚሆኑ የተለያዩ አገራት አትሌቶች መካከል ለከፍተኛ ውጤት ከሚጠበቁት ውስጥ ኢትዮጵያዊን አትሌቶች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በውድድሩ ውጤታማ ለመሆኑ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ ዮሐንስ እንግዳ ለኢዜአ እንደገለጹት ለሻምፒዮናው አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች መምረጥና ማዘጋጀት ከዝግጅቶች መካከል አንዱ መሆኑን ነው። 

የአትሌቶች ምርጫ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሕግና አሰራር በሚቅደው መሰረትና በፌዴሬሽኑ መመሪያና ደንብና መሰረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የዓለም አትሌቲክስ በዚህ ዓመት በ10 ሺህ ሜትር የሚካፈሉ አትሌቶች የሰዓት ማሟያ (ሚኒማ) ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍ እንደተደረገ ገልጸዋል።

በ10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን የሚወክሉ የአትሌቶች ሚኒማ ምርጫ በሃዋሳ ላይ ለማካሄድ እቅድ የነበረ ቢሆንም አትሌቶች ሰዓቱን ለማምጣት ስለሚቸገሩ የቦታ ለውጥ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአትሌቶች የሰዓት ማሟያ የማጣሪያ ውድድር በስፔን አገር ማላጋ ከተማ እንደሚካሄድ ነው የገለጹት። 

ከዚህ በፊት ይህን የማጣሪያ ውድድር በኔዘርላንድስ ሄንጌሎ ላይ ይደረግ እንደነበርም አስታውሰው በዚህ ዓመት ግን  ውድድሩን ለማካሄድ ፍቃድ እንዳላገኙ እና በዚህ ምክንያት በስፔን የማጣሪያ ውድድሩ  እንደሚካሄድ ተናግረዋል። 

በማራቶን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችም በዚህ ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚደረጉ ነው የገለጹት።

በሌሎች ርቀቶች ላይ አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች ምርጫ በተለያየ ውድድሮች ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት እንደሚመረጡ አቶ ዮሐንስ አመልክተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም