በምሥራቅ ጎጃም በመስኖ ከለማው የበጋ ስንዴ ከ881 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ - የዞኑ ግብርና መምሪያ

108

ደብረ ማርቆስ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ):- በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጋ ወራት በመስኖ ከለማው የስንዴ ማሳ እስካሁን ከ881 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

በመምሪያው የመስኖ ልማት የሥራ ሂደት ቡድን መሪ  አቶ ሃብታሙ አሕመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ አርሶ አደሮችንና ባለሙያዎችን ያሳተፈ የተቀናጀ ርብርብ ተደርጓል። 

በዚህም  በዘንድሮው በጋ ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ21 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ መልማቱን ገልጸዋል።


 

ከለማው ማሳ ላይም ከ920 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ881 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል። 

በዞኑ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ከተጀመረ ሁለት ዓመታት እንደሆነው የተናገሩት የቡድን መሪው፣ በዚህ ዓመት የለማው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ17 ሺህ ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።   

የበጋ ስንዴ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮች ከ6ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ጥቅም ላይ ማዋላቸውን አስረድተዋል።

በልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል በእነማይ ወረዳ የማህበረ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋው ገላዬ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ ግማሽ ሄክታር መሬት በማረስ ከ23 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ካመረቱት ስንዴም ከ15 ኩንታል በላይ የሚሆነውን ሸጠው ከ60 ሺህ ብር በላይ እንዳገኙ አስታውቀዋል።

የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አስናቀ እንደግ በበኩላቸው በበጋ ስንዴ ልማቱ በመሳተፍ ምርታማነታቸውን እንዳሳደጉ ተናግረዋል። 

ወደ መስኖ ልማቱ ለመግባት እየተጠራጠሩ እንደ ጀመሩ ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ ከሩብ ሄክታር በላይ ማሳ በማረስ 18 ኩንታል ምርት በማግኘታቸው ግን ጥርጣሬያቸው እንደተወገደ ገልጸዋል።

 

   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም