ቀጥታ፡

በየቦታው በሚጣል ኘላስቲክ አማካኝነት  የሚከሰት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያሻ ተጠቆመ

ሠመራ ግንቦት 28 /2015(ኢዜአ)፡- በየቦታው በሚጣል ኘላስቲክ አማካኝነት  የሚከሰት የአካባቢ ብክለትን  ለመከላከል የምርምር ተቋማትን ጨምሮ የሁሉም ቅንጅታዊ ተሳትፎ እንደሚያሻ ተጠቆመ።

የዓለም የአካባቢ ቀን ዛሬ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ በፓናል ውይይት፣ በአካባቢ ፅዳትና በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከብሯል።
 

የአፋር ክልል የአካባቢ ጥበቃ ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤  አካባቢያችንን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የኘላስቲክ ቆሻሻን ከምንጩ  ጀምሮ ጥቅም እስከሚውሉበት ድረስ በመከታታል መቀነስ ይኖርብናል ብለዋል።

ኘላስቲኮች በቀላሉ የማይበሰብሱና እስከ አንድ ሺህ ዓመታት እንደሚቆዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ያወሱት ኃላፊው፤ በኘላስቲኮች የተሸፈነ መሬት ወደ ውስጡ የዝናብ ውሃና አየር ስለማያስገባ  ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስበትና እንስሳት ላይም ጉዳት እንደሚያስከትል ጠቅሰዋል።
 

በመሆኑም በየቦታው ሚመጣል ኘላስቲክ አማካኝነት  የሚከሰት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል መላው  ህብረተሰብ፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ የምርምር ተቋማትና የሌሎችም አካላት ቅንጅታዊ ተሳትፎ እንደሚያሻ ጠቁመዋል።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን አቶ ሃቢብ መሃመድ  በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ  የሚያግዙ የምርምር ስራዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ከኘላስቲኮች የፀዳ አካባቢን ለመፍጠር ለህብረተሰቡ  የግንዛቤና የማንቃት ተግባራት እንደሚያስፈልግ  ገልጸዋል።

ተቋሙ በየዓመቱ የማህበረሰብ አገልግሎት ሳምንት  እንዳለውና  ከዚህ ውስጥ የአካባቢ ፅዳት ቀን በመርሃ ግብሩ አካቷል ብለዋል።

በቀጣይም ለመፍትሄዎቹ የተጠናከረና የተቀናጀ ስራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"ከኘላስቲክ ብክለት የፀዳ አካባቢ እንፍጠር"በሚል መሪ ሃሳብ  የተከበረው የዓለም የአካባቢ ቀን መርሃ ግብርን ያሰናዱት የአፋር ክልል የአካባቢ ጥበቃ ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮና የሠመራ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመሆን ነው። 

የቢሮውና የዩኒቨርሲቲው  አመራሮች ፣ተማሪዎችና ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም