ኢትዮጵያ እና ብራዚል ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ

289

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ብራዚል ያላቸውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ መክረዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ጊዜው አሁን መሆኑን የገለፁ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያ በብራዚል ዳግም ኤምባሲዋን መክፈቷም ግንኙነቱን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ብራዚል በኢትዮጵያ በዘላቂ የደን ልማት አስተዳደር በጥጥ ምርት እና በአፈር ጥበቃ ላይ ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለቸው መልካም አበርክቶም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ አቪዬሽን፣ ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በአከባቢ ጥበቃ፣ በማዕድን እና ኢነርጂ ዘርፎች ከብራዚል ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠውላቸዋል።

የብራዚሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ በበኩላቸው፣ አገራቸው በስፖርት እና የተለያዩ መስኮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው ፤ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል ቀጣይ የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድም መግባባት ላይ መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም