የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ህይወት እያሻሻለ ነው

110

ሰቆጣ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)  በአማራ ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት በማሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

በክልሉ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚተገበርባቸው 17 ከተሞች የስራ ሃላፊዎች በሰቆጣና ላለቢበላ ከተሞች በከተማ ፕሮግራሙ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል። 

የክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት  ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሱሌማን እሸቱ በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት በተለይም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ከተሞች መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው።

በዚህም በላሊበላና በሰቆጣ ከተሞች በፕሮግራሙ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን እንቅስቃሴ በማስጎብኘት የተሞክሮና ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ገልጸዋል። 

በመስክ ጉብኝቱም በክልሉ ፕሮግራሙ የሚተገበርባቸው ከ17 ከተሞች  የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸው ግቡን ለማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል። 

በክልሉ በልማታዊ ሴፍቲኔት ከታቀፉት ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ 80 ሺህ የሚሆኑት በከተሞች ፅዳትና ውበት ዘርፍ በመሰማራት የከተሞችን ገጽታ በመገንባት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። 

በተጨማሪ የገቢ ማስገኛ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም አነስተኛ ንግድ ስራዎች በመሰማራት በአጭር ጊዜ ኑሯቸው እንደሚሻሻል በሰሩት ስራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ሱሌማን ገለፃ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት በማሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።  

የጎንደር ከተማ የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሃድያ መሃመድ እንዳሉት የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ከ2014 ዓ.ም ታህሳስ ወር ጀምሮ በከተማቸው መተግበር መጀመሩን ተናግረዋል። 


 

በአሁኑ ወቅትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ  ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች በአካባቢ ልማትና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማከል። 

በመሆኑም የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የስራ ባህልና የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሃድያ የገለፁት። 

የደሴ ከተማ የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሙሴ በበኩላቸው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መተግበር ከተጀመረ ወዲህ የተጠቃሚው ህይወት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል። 

በዚህም በፕሮግራሙ በመጀመሪያው ዙር ታቅፈው የነበሩ 15 ሺህ 547 ዜጎች ማስመረቅ መቻሉን ጠቁመው በሁለተኛ ዙርም 4 ሺህ 767 ዜጎች በከተማቸው የአካባቢ ልማትና እንክብካቤ ላይ እየሰሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በተለይም በመጪው ክረምት በከተማዋ የጎርፍ አደጋ እንዳያጋጥም ቦዮችን በማጽዳት፣ የፈረሱትን በመጠገንና አዳዲስ መከላከያ ቦዮችን በመገንባት የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ መስራታቸውን አስረድተዋል።

ለፕሮግራሙ ስራ ማስኬጃ በተያዘው ዓመት የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ በክልሉ በ17 ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም