የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ለቱሪስት መዳረሻ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል- ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ለቱሪስት መዳረሻ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል- ቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015 (ኢዜአ) የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ለቱሪስት መዳረሻ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።
በሚቀጥለው ዓመት የሚጠናቀቀው የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት፤ ቀጣይ ምዕራፍ እንዲኖረው ለማስቻል፤ ፕሮጀክቱን ለሚደግፈው የፈረንሳይ መንግስት ጥያቄ መቅረቡንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ከቱሪዝም ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክትን አሁናዊ የአፈጻጸም ደረጃ ጎብኝቷል።
'ዘላቂ ላሊበላ' ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቅዱስ ላሊበላ ታሪካዊ ስፍራን በ2011 ዓ.ም መጋቢት ወር ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ለታሪካዊ ቅርሱ ዕድሳትና ጥገና ለማከናወን የተወጠነ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት የቅርስ ጥገና፣ ስዕላትና ቅርጻ ቅርጾችን ማስተካከል፣ የቅርስ ስራ አመራርን ማሻሻል፣ አርኪዮሎጂ ስራና የዲጂታል የመረጃ ቋት ማቋቋም የሚሉ አምስት ዘርፎችን ያቀፈ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ ከቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች አንዱ የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት 22 ዓበይት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በኮቪድ 19 እና በጦርነት ምክንያት ቢጓተትም፤ በዚህ ዓመት በገጸ ምድር ማስተካከል፣ የድልድይ፣ የብራና መጻሕፍትን ወደ ዲጂታል የመለወጥና ሌሎች ተግባራት አበረታች ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እና ሌሎች የቅርስ ጥበቃና ልማት ስራዎች የቱሪስት መዳረሻ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቸውንም ነው የገለጹት።
በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ የሚከናወነው የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት በኋላ የሚጠናቀቅ በመሆኑ፤ ሌሎች ቀጣይነት ያላችው ስራዎችንም ለማከናወን ፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ እንዲኖረው ጥያቄ አንስተዋል።
በዚህም በፈረንሳይ በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንደተሰጠ ገልጸው፤ ቀጣይ የፕሮጀክቱን ትግበራ በተመለከተም ሚኒስቴሩ እንደሚያሳውቅ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ የጥገና፣ የመዳረሻ ልማትና የቱሪስት መዳረሻን ምቹ የማድረግ ስራዎች ትልቅ እመርታ ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
በህዝብ ተወካየች ምክር ቤት የላስታና አካባቢው ህዝብ ተወካይ ቅድስት አርዓያ፤ ፕሮጀክቱ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠርና በዕውቀት ሽግግር አበረታች ውጤቶችን ማምጣቱን ገልጸዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ደብር የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዲያቆን መኮንን ገብረ መስቀል፤ ፕሮጀክቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በቱሪስት ፍሰት መቀነስ ምክንያት ችግር ውስጥ ለነበሩ በርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረገ አንስተዋል።
እንደ ዲያቆን መኮንን ገለጻ፤ የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀከት አፈጻጸም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ጉልህ መሻሻል አሳይቷል።
የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ኪዳኔ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ስራ በጦርነት ቢስተጓጎልም ባለፉት ሶስት ወራት በአምስቱም ዘርፎች በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም የቱሪስት ፍሰት መሻሻል በጎ አስተዋጽኦ ማድረጉን በማንሳት እስካሁን ፕሮጀክቱ ከ1 ሺህ 400 በላይ ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት።
በቀጣይም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ መሰረት ቀሪ ስራዎችን ለመጨረስ ያለውን ሙሉ አቅም በመጠቀም እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት አማካይነት የሁለት ዓመታት ዝግጅት የፈጀ የላሊበላ መካነ ቅርሶችን የሚያሳይ በቨርቹዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂ የታገዘ ቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ክፍት ሆኗል።