አውደ-ርዕዩ የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል ውጤት የተገኘበት ነው - የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015  (ኢዜአ)፦ የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ የዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል ውጤት የተገኘበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የነበረው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ ከ88 ሺህ በላይ ሰዎች መጎብኘት መቻላቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።  

በሳይንስ ሙዚየም ለአንድ ወር “ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ” በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ የነበረው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ በትላንትናው እለት ተጠናቋል።

አውደ-ርዕዩ የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል ውጤት የተገኘበት ሆኖ መጠናቀቁ ተገልጿል። 

ትላንት በተካሄደው የአውደ-ርዕዩ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓትም አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል። 


 

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ የተሳካ ዓላማዎቹና ግቦቹን ያሳካ ነው።

በዚህም የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል ውጤት የተገኘበት አውደ-ርዕይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብርናው ከየት ተነስቶ የት እንደ ደረሰ፣ ግብርናውና የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ፈጠራዎች የደረሱበትን ሁኔታ ለማሳየት በተካሄደው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ ጠቃሚ ውጤቶች መገኘታቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።   


 

ከግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ ጎን ለጎንም የስንዴ ልማት ውጤታማነት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎችና ዲጂታል ግብርና ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶችም እንደተካሄዱ ዶክተር ግርማ አመንቴ አክለዋል።

አውደ-ርዕዩ በተለይም የግብርናው ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ የተመላከተባቸው፣ ዘርፉን ማሳደግና የተገኙ ስኬቶችን ማጠናከር የሚያስችሉ አራት አውደ-ጥናቶች መካሄዳቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። 

ሌሎች ግብርናውን አጋዥ የሆኑ ዘርፎችን ያካተተ አውደ-ርዕይ በቋሚነት እንዲካሄድ ጥያቄዎች መነሳታቸውንም ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን ለሰጡት ሽፋን ምስጋና ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ የተሻለ የግብርና አውደ-ርዕይ ለማዘጋጀት በቂ ልምድ እንደተገኘበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም