በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ ይገባል-አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ

166

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ እንደሚገባ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ ገለጹ።

በኩዌት የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሳሌም አብደላህ አል-ጀብር አል-ሳባህ አቅርበዋል።

በዚህ ወቅት በነበራቸው ውይይትም በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ ይገባል ሲሉ አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ ገልጸዋል።

በኩዌት በሚኖራቸው ቆይታም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር አንደሚሰሩና ለዚህም የኩዌት መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።


 

የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሳሌም አብደላህ አል-ጀብር አል-ሳባህ በበኩላቸው ኩዌት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ባለ-ብዙ ወገን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አሰታውቀዋል።

አምባሳደር ሰይድ በኩዌት በሚኖራቸው ቆይታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ለሚሰሩት ስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

አምባሳደሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተላከ መልዕክት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም