በስርአት አልበኞች ላይ እየተወሰደ ያለው የህግ ማስከበር እርምጃ ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ ትብብር ማድረግ አለበት--አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ 

183

ሰቆጣ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) መንግስት በስርአት አልበኞች ላይ እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ ከዳር እንዲደርስ ህዝቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለበት ሲሉ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ ዓመት 25ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፣ አገራዊ ሰላምን በማረጋገጥ የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስ ሁሉም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ አለበት።

ለውጡን የማይፈልጉ አንዳንድ ሃይሎች ሃሳብን በምክክር ማሸነፍ ሲያዳግታቸው እየሄዱበት ያለው   ፓለቲካ ተቀባይነት የለውም፤ ህዝብንም ለከፋ ችግር ያጋልጣል ብለዋል። 

መንግስት በስርአት አልበኝነት የሚንቀሳቀሱትን አካላት ስርዓት ለማስያዝ እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር እርምጃ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደማይለየው ገልጸዋል።

የህግ ማስከበር እርምጃው ግቡን እንዲመታም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበትም አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል። 

በዞኑ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ወደቄያቸው መመለሳቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፣ በአካባቢውም ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

ወደቄያቸው ለተመለሱ ወገኖች ባሉበት የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማት አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ እንዲያደርጉም በምክር ቤቱ ስም ጠይቀዋል። 

የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ህብረተሰቡ ወደመደበኛ ህይወቱ በመመለስ የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንዲያነቃቃ በተሰራው ሥራ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይሄ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመለክተዋል። 

ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የአስፈፃሚ አካላትን ዕቅድ አፈጻጸም እንቅስቃሴ ለማወቅ በመስክ ምልከታ ጭምር እያደረገ ያለው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታይቱ አመለክተዋል። 

በዞኑ እየተስተዋለ ባለው ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ብልሹ አሰራርና ሌብነት ህዝቡ እየተማረረ በመሆኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምንና የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን እቅድ ክንውን እንደሚገምግም ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም