11ኛው የአማራ ክልል መስሪያ ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በደሴ ከተማ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
11ኛው የአማራ ክልል መስሪያ ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በደሴ ከተማ ተጀመረ
ደሴ ግንቦት 27/2015(ኢዜአ)፡-ህብረተሰቡ በስፖርት የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በማጠናከር ለአገር ሰላምና አንድነት በጋራ መስራት እንዳለበት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
11ኛው የአማራ ክልል መስሪያ ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ዛሬ በደሴ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ውድድሩን ያስጀመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደገለጹት ስፖርት ጤናማ፣ ብቁና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ጉልህ ሚና አለው።
በመሆኑም ህብረተሰቡ አንድነቱን ከመጠበቅ ባለፈ በስፖርት የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በማጠናከር ለአገር ሰላም በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ውድድሩ የመንግስት ሠራተኛውን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ በየተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ለህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ መነቃቃትን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
ከስምንት በላይ ክልሎች የሚሳተፉበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንግስት ሠራተኞች ስፖርታዊ ውድድርም ከሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በደሴ ከተማ እንደሚካሄድና ለእዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው፣ "በክልሉ ሠራተኞችን በስፖርት ውድድር በማሳተፍ ለህብረተሰቡ ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ስፖርት አካላዊ ብቃትንና ጤንነትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም በየአካባቢው ስፖርትን ማዘውተር እንዳለበት መክረዋል።
ዛሬ የተጀመረው የስፖርት ውድድር እስከ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚዘልቅ የገለጹት ኃላፊው፣ "በውድድሩም ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ ከ800 በላይ ሠራተኞች ይሳተፋሉ" ብለዋል።
እንደሃላፊው ገለጻ፣ ውድድሩ እግር ኳስንና መረብ ኳስን ጨምሮ በ5 የስፖርት ዓይነቶች ነው እየተካሄደ ያለው።
ዓላማውም ጤናማና አምራች ሠራተኛ መፍጠር፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከርና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚካሄደው የመስሪያ ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መምረጥ መሆኑን አቶ እርዚቅ አስረድተዋል።
ባህር ዳር ከተማን ወክለው በእግር ኳስ ከሚሳተፉ ሠራተኞች መካከል አቶ ሀይለየሱስ ሙሉዓለም በበኩላቸው "በውድድሩ ጤናችንን ከመጠበቅና ግንኙነታችንን ከማጠናከር ባለፈ ሰላማችንን እንጠብቃለን" ብለዋል።
"በእግር ኳስ ውድድር አሸናፊ በመሆን ክልሉን ለመወከል ቅድመ ዝግጅት አድርገን ነው የመጣነው፤ ለማሸነፍ የምንችለውን ያህል እንጥራለን" ሲሉም ገልጸዋል።
በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ ደሴ ከተማን የወከለው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባህር ዳር ከተማን ከወከለው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በአግር ኳስ ጨዋታ ውድድር አካሂደዋል።
በማስጀመሪያ ስነስርአቱ ላይም የፌዴራል የክልል፣ የደቡብ ወሎ እና የደሴ ከተማ ሥራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።