በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲመጣ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ተባብሮ መስራት ይገባል---ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲመጣ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ተባብሮ መስራት ይገባል---ምሁራን
ደሴ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና አገራዊ አንድነት እንዲመጣ ሁሉም ለሀገራዊ ምክክሩን ስኬታማነት ተባብሮ መስራት እንዳለበት ምሁራን ገለጹ።
በዘላቂ ሰላም፣ ሰብዓዊ መብትና የሀገራዊ ምክክሩ አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መድረክ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ "የምክክሩ አካታችነት ለውጤታማነት" በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ አቶ ዘላለም እሸቱ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና አንድነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍ ያለ ነው።
በመሆኑም ሁሉም በየደረጃው ሀገራዊ ምክክሩን በመደገፍ ለስኬታማነቱ ሊረባረብ እንደሚገባ ጠቁመው፣ በምክክሩ ከራስ ስሜትና ፍላጎት ይልቅ የአገርን ጥቅምና ሉዓላዊነት ማስቀደም እንደሚገባ መክረዋል።
ለምክክሩ ስኬታማነት በተለይ ምሁራን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ጥናት በማድረግና በመድረኩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው፣ በእዚህ በኩል የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ትክክለኛ የህዝብ አጀንዳን በማንሳትና ሀሳብ በመስጠት ወደጋራ መግባባት መምጣት እንጂ ከምክክር መድረኩ ራስን ማግለል ለራስም ለሀገርም አይጠቅምም ብለዋል።
ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገራዊ ምክክሩ ማሳተፍ አግባብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘላለም፣ በአገራዊ ምክክሩ ድምጹ የማይካተት የህብረተሰብ ክፍል መኖር እንደሌለበት ተናግረዋል።
"ሁላችንም የሀገሪቱን ነበራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የሚጠበቅብንን ማድረግ አለብን" ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ጎራው ናቸው።
በተለይ ለአንድነታችን፣ ለሰላማችንና ለጋራ እድገታችን ተስፋ የሆነው ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ሀሳብ በመስጠት፣ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ በማስተባበርና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ሀገራዊ ግዴታን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"እኛ ምሁራን የሚጠበቅብንን ለማድረግ ዝግጁ ነን" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በሀገራዊ የምክክሩ ተግባብቶ አገራዊ እንድነትና ሰላምን ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
"ይህን ማድረግ ካልተቻለ ወደ ማንወጣው ቀውስና ውስብስብ ችግር ልንገባ ስለምንችል መጠንቀቅ ይኖርብናል" ሲሉም አክለዋል።
ቀውስ ውስጥ የገቡ አንዳንድ አገራት ዜጎቻቸው ወደተለያዩ ሀገራት ተሰደው ለልመና መዳረጋቸውንና ኑሯቸውም መመሰቃቀሉን ምሁሩ አስታውሰዋል።
ሀገር ከሌለ ሁሉም ነገር ይቀራል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን፣ አሁን ያለውን ሰላም በመጠቀም ለህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
መንግስትም የሰላም አማራጮችን ማስፋት እንዳለበት ገልጸው፣ ህብረተሰቡም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስበዋል።
"ሁሉም ለሀገራዊ ምክክሩ ምን ልደግፍ፣ ምንስ ላግዝ፣ የኔ ድርሻስ ምንድነው ብሎ በማሰብ ለስኬታማነቱ የበኩሉን መወጣት አለበት" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስ ናቸው።
ምክክሩ ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና ልማት ወሳኝ መሆኑ ላይ ሁላችንም ተግባብተን ወደስራ ገብተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለሀገር ሉአላዊነትና ዘላቂ ሰላም ሲባል ልዩነቶችን በማጥበብ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ በመሆኑ ደምጹን ማሰማትና ለውሳኔው ተገዥ መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሚወክለን ውሳኔ እንዲተላለፍ ከወዲሁ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ምሁራንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።