ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ ያደረገበትን ድል አስመዝግቧል

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በ17ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ ለሀዲያ ሆሳዕና የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የሀዲያ ሀሳዕናው ቃለአብ ውብሸት በ31ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል።


 

ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና በ39 ነጥብ ደረጃውን ከ7ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ከፍ አድርጓል።

በአንጻሩ ከፕሪሚየር ሊጉ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታ በመቻል እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይደረጋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም