ቀጥታ፡

በዘጠኝ ወራት ለ609 ስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ ተደርጎ አንድ አትሌት መጠቀሙ ተረጋግጧል

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ):- በዘጠኝ ወራት ለ609 ስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ ተደርጎ አንድ አትሌት ተጠቅሞ በመገኘቱ   ቅጣት እንደተላለፈበት  የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ገለጸ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርታዊ ውድድሮች ኃይል የሚጨምሩ አበረታች የተከለከሉ ቅመሞችን መጠቀም የዘርፉ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መጥቷል።

በኢትዮጵያም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የስፖርት አበረታች ቅመሞች መከላከልና ቁጥጥር ሥራ እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 በይፋ ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል፤ አበረታች ቅመም በስፖርት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈ-ብዙ የቁጥጥርና መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች አስደናቂ የሚባሉ ውጤታማ ሥራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል ነው ያሉት።

በዚህም የስፖርተኞች፣ የአሰልጣኞች ሌሎች የስፖርት  ቤተሰቦች በሰፊው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ለ3 ሺህ አትሌቶችና የስፖርት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በተለያዩ የውድድር መድረኮችም ከ16 ሺህ ለሚልቁ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በዘጠኝ ወራት ለ609 ስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ ተደርጎ አንድ አትሌት አበረታች መድኃኒት ተጠቅሞ በመገኘቱ መቀጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ካሉ አቻ ተቋማት ጠንካራ ከሚባሉት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የበለጠ የማጠናከር ዕቅዶችም አሉ ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ቦንካ፤ በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ማድነቃቸውንም አስታውሰዋል። 

የመፈጸም አቅምን በቀጣይነት ለማጠናከርና በኢትዮጵያ የአበረታች ቅመሞች የምርመራ ማዕከል እንዲኖር ጭምር ዕቅድ ተይዞ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት መኖራቸውንም ነው የገለጹት።

አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አትሌቶች ላይ ከሚደረገው ምርመራ በተጨማሪ ከጀርባ ያሉት ባለድርሻ አካላት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም