ቀጥታ፡

የቀቤና ብሄረሰብ የታሪክ፣ የቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው

ወልቂጤ፣ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) 3ኛው ዙር የቀቤና ብሄረሰብ የታሪክ፣ የቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም በወልቂጤ ከተማ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ እንደገለጹት፤ "ታሪኩን የማያውቅ ህዝብ ዛሬን መረዳት አይችልም"።

"ዛሬን መረዳት የነገን አቅጣጫ ለማወቅ ወሳኝ ነው" ያሉት አቶ ገመቹ፤ ትውልዱ የአገሩን ታሪክ እንዲገነዘብ ይበልጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የቀቤና ወረዳ ህዝቡ ታሪኩን እንዲረዳ ለማስቻል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።


 

'የቀቤና ህዝብ ታሪክ በአገር ግንባታ' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ሀይሩ አህመዲን በበኩላቸው በአገር ግንባታ ሂደት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉም ለፍቶ የገነባት አገር መሆኗን በመገንዘብ አንድነቷን ጠብቆ ለማቆየት በጋራና በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የቀቤና ብሄረሰብ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በመተባበር ለአገር አንድነት መጠናከር የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀቤና ልማት ማህበር በወልቂጤ ከተማ የተገነባው የቀቤና ባህል ማዕከል ትናንት በደማቅ ሥነ ስርዓት መመረቁን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም