ህብረተሰቡ መደበኛ ህይወቱን ያለስጋት መምራት እንዲችል የጸጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ ይገባል-- መምሪያው

234

ሆሳዕና ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) ፡-ህብረተሰቡ መደበኛ ህይወቱን ያለስጋት መምራት እንዲችል የጸጥታ አካላት ሙያዊ ስነምግባር ተላብሰው የተጣለባቸውን ሀላፊነት በተሻለ ብቃት ሊወጡ እንደሚገባ የሀድያ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

በሀድያ ዞን ፖሊስ መዋቅር ላይ የተስተዋሉ ጉድለቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ዞን አቀፍ የአመራር ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሀድያ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የጸጥታ አካላት የህዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሃላፊነት አለባቸው።  


 

በመሆኑም ህብረተሰቡ መደበኛ ህይወቱን ያለስጋት መምራት እንዲችል የጸጥታ አካላት ሙያዊ ስነምግባር በመላበስ ሃላፊነታቸውን በተሻለ ብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ስነምግባርን ተላብሶ አገልግሎት በመስጠት በኩል በዞኑ ባሉ የጸጥታ መዋቅሮች የተስተዋሉ መጠነኛ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው፣ ዞኑ ችግሮችን ለይቶ ለማረም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የግምገማ መድረኩም የዜጎችን ደህንነትና ሰላም በማስጠበቅ ተግባር በተለይ በአንዳንድ የጸጥታ አካላት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ በተለይም በሆሳዕና ከተማና በሌሎች አካባቢዎች ከንጥቂያ፣ ዝርፊያና መሰል እየተበራከቱ ያሉ ወንጀሎችን ለማስቀረት የሚያስችል የጋራ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡትን በመለየት አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወሰድና ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ዋና ሳጅን ተሾመ ባቲሶ በበኩላቸው፣ የዞኑ የፖሊስ መዋቅሮች በወንጀል ቅድመ መከላከልና ፍትሀዊ አገልግሎት በመስጠት በኩል ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"ከህዝብና ከመንግስት የተሰጠን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲገባ ኃላፊነትን ወደጎን በመተው የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሰሩ የፖሊስ አባላት ስለመኖራቸው በተለያየ መንገድ ለማወቅ ተችሏል" ብለዋል።

ባልተገባ ተግባር በመሳተፍ ላይ የሚገኙ አባላትን በመለየት ተገቢ የሆነ እርምትና እርምጃ ለመውሰድ የግምገማ ውጤት እየተጠበቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ሳህሉ ኃይሌ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ፖሊስ የአካባቢንና የማህበረሰቡን ሰላም የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ይሁንና ፖሊሳዊ ስነ ምግባርንና መርህን ተከትሎ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል።

"የማህብረሰቡን ሰላም አጠናክሮ የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት በኩል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የመድረኩ አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

የፀጥታ አካላት ሙያዊ ስነ ምግባር በመላበስና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ለአካባቢ ስጋት የሆኑ የጸጥታ ችግሮችን ለማስቀረት መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ በመምሪያው የስታፍ ዲቪዥን ኃላፊው ኢንስፔክተር አብርሃም ቀጭኔ ናቸው።

እንደእሳቸው ገለጻ፣ ማህበረሰብን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ተግባር የማህበረሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በመድረኩ በዞኑ ከሚገኙ ከሁሉም የገጠር ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የሰላምና ፀጥታና እንዲሁም የፖሊስ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም