በአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ሰልጠና ላይ የሚገኙ እጩ የፖሊስ መኮንኖች በደብረ ማርቆስ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ቤት ገንብተው አስረከቡ

142

ደብረ ማርቆስ ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) በአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ሰልጠና ላይ የሚገኙ እጩ የፖሊስ መኮንኖች በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሶስት አቅመ ደካሞች ቤት ገንብተው አስረከቡ።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ተወካይ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ህዝባዊነትን የተላበሰ ፖሊስ የህብረተሰቡን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር በሰብአዊነት ተሳትፎ የማድረግ ሃላፊነት አለበት።

በኮሌጁ የሚሰለጥኑ የፖሊስ እጩ መኮንኖች ካላቸው በማዋጣት የማህበረሰብን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የልማት ስራዎችን መስራታቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ ካላቸው በማዋጣት በደብረ ማርቆስ ከተማ ሶስት ቤቶችን ገንብተው በማስረከብ አቅመ ደካማ ግለሰቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራታቸውን ተናግረዋል።

ቤቶቹ ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸው የገለጹ ሲሆን ሰልጣኞቹ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት።

የፖሊስ እጩ መኮንኖቹ ከዚህ በተጨማሪም የደብረ ማርቆስ ከተማ ጽዳትና ውበት በመጠበቅ በኩል ጉልህ ሚና እየተጨዋቱ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የመንቆረር ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ አስታራቂ መኩሪያው እንዳሉት እጩ የፖሊስ መኮንኖች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎችን መኖሪያ ቤት ግንባታና እድሳት ላይ እየተሳተፉ ነው።

ከፍለ ከተማውም በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ4 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ከ60 በላይ ቤቶች በማስገንባት አሁን ላይ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

እጬ መኮንን አስቻል ኪዳኔ፣ ''ከምናገኛት ቀንሰን ለችግረኛ ግለሰቦች ቤት መስራታችን የህዝብ ልጆች መሆናችንን ለማሳየት ነው'' ብሏል።

በቀጣይም በኮሌጁ እስካሉ ድረስ የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል።

እጩ መኮንን አብዱ ባልዲቾም እንዲሁ የአቅመ ደካሞችን እና የችግረኞችን ቤት መገንባት ከፍተኛ የአእምሮ እርካታን የሚፈጥር ነው ብሏል። 

አሁን የተገነቡት ቤቶች መጀመሪያቸው እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ ገልጸው ለወደፊትም የማህበረሰብ አገልግሎታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም