የኢትዮጵያን መስህቦች የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው- ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን መስህቦች በተለያዩ አማራጮች የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

"ላሊበላ በእምነት የታነፀ" በሚል መሪ ሀሳብ የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ የቋሚ ዐውደ ርዕይ በላልይበላ ከተማ ተከፍቷል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ በቱሪስት መዳረሻ ታሪካዊ ቅርሶች ዙሪያ ዕሴት የሚጨምሩ ተግባራትን በማከናወን ተወዳዳሪ መዳረሻነት እና ማህበራዊ አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በእንጦጦ ፓርክ የላልይበላ ቨርቹዋል ሪያሊታ ዐውደ ርዕይ ተከፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኝታቸውን አስታውሰው በላልይበላ ደግሞ ተመሳሳይ አውደ ርእይ መከፈቱን ጠቅሰዋል።

በዩኔስኮ የተመዘገቡ የዓለም ቅርሶችን ማልማትና መጠበቅ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን የመጠበቅና የቱሪስት መዳረሻነቱን የማልማትና የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን መስህቦች የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የጎንደርና የጅማ አባጅፋር አብያተ መንግስታት ዕድሳትንም ለአብነት ጠቅሰዋል። 

በዘርፉ አቅም ለመገንባት የሰው ኃይል ስልጠና፣ የቱሪስት አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሆቴልና ቱሪዝም ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በላሊበላ የተለመዱ የቱሪዝም ሀብቶችን ማሳየት ብቻ ሳይሆን የጎብኝዎችን ቆይታ የሚያራዝም የጉብኝት ፓኬጅ በመቅረፅና እሴት በመጨመር ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችልና አካባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ 'የላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክት' እየተተገበረ መሆኑንም አንስተዋል። 

የጊዜ ገደቡ ለመጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው የዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ቀጣይ ምዕራፍ እንዲኖረውም ጠይቀዋል። 


 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሕይወት ኃይሉ፤  ቅርሶች ታሪክን ለመዘከር፣ ተፈጥሮና አካባቢን ለመረዳት ፣የመረጃ ምንጭ በመሆንና የገቢ ምንጭነታቸው የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

ባለስልጣኑ ቅርሶች ለታሪክ ምስክርነት እንዲውሉ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ከጉዳት የመጠበቅ፣ የማጥናትና ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ጥቅማቸውን የማሳደግና ተደራሽ የማድረግ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፈረንሳይ ልማት ኤጄንሲ ድጋፍ በ22 የትኩረት መስኮች ተለይቶ የሚሰራው 'የላልይበላ ዘላቂ ልማት' ፕሮጀክት ትግበራም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የላሊበላ ቋሚ ዐውደ ርዕይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና የጎብኚዎችን ቆይታ የሚያራዝም መሆኑን ገልፀው፣ በቀጣይም በሌሎች ቦታዎችም  ይከፈታል ብለዋል። 

የቅርስ መጠበቅና መንከባከብ የዜግነት ኃላፊነት ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ዕድሳትና ጥገና እንዲሁም የቅርሶችን ጊዜያዊ መጠለያ የማንሳት ስራዎች በጥንቃቄ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ተወካይና የኤምባሲው የባህል ካውንስለር ሶፊ ማካሜ፣ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀው የኢትዮ ፈረንሳይ ወዳጅነትና ትብብር በታሪካዊ ቅርሶች ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በታሪካዊ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተጨባጭ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢኒሼቲቭ ወደ ትግበራ የገባው የላልይበላ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክት፣ የብሔራዊ ሙዚየም መልሶ የማደራጀት እንዲሁም የብሔራዊ ቤተ መንግስት ዕድሳትም ከትብብር ስራዎች ለአብነት አንስተዋል። 

የላሊበላ ታሪካዊ ቅርስ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ፋይዳ እየሰጠ ያለ ሃብት በመሆኑ የአካባቢውና የውጭ ባለሙያዎችን አቅም በመደመር የቅርሱን ቀጣይነት የማረጋገጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የላሊበላ ቅርስ መጠበቅና መንከባከብ የቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልፀው፤ ለዚህም የላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክት ቅርስን ለትውልድ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ የድርሻዋን እያበረከተች መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ትግበራና ቋሚ ዐውደ ርዕዩ ለኢትዮጵያና ለዓለም አቀፍ ጉብኝዎች ታሪካዊና መንፈሳዊ መልኮች በመዘከር ታሪካዊ አረዳድ የሚያጎለብት፣ የወደፊት የመረጃ ቋት ግንባታ መሰረት የሚሆንና ለአካባቢው ማህበረሰብ አካታች ልማት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።  

በላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክት ትግበራ ሂደት ትብብር ያደረጉ አካላትን አመስግነው፤ ለኢትዮጵያ ቅርሶች መጠበቅ ፈረንሳይ እገዛዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም