የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

378

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት ሀዲያ ሆሳዕና ቀድሞ ከሊጉ መውረዱን ካረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ከቀኑ 7 ሰአት ላይ ይጫወታል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሀዲያ ሆሳዕና በ36 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃን ይዟል።

ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በአንጻሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በ27ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የመጨረሻው ጨዋታ በመቻልና ባህር ዳር ከተማ መካከል ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ መቻል በ34 ነጥብ 11ኛ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በ50 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

መቻል ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሲሸነፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ባህር ዳር ከተማ ጨዋታውን ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ ያደርጋል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 3 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ወልቂጤ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሃዋሳ ከተማ ቆይታ እንደሚጠናቀቅ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ከ28ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ያሉ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ከሰኔ 1 እስከ ሐምሌ 1 2015 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም