በጋምቤላ ክልል የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል  እንቅስቃሴ ተጀመረ

145

ጋምቤላ ግንቦት 26 /2015(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር  የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የተማሪ ወላጆች ህብረት ሰብሳቢ በበኩላቸው፤ በየደረጃው የሚገኙ የተማሪ ወላጅ ህብረት አደረጃጀቶችን በማጎልበት ለትምህርት ጥራት መሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤  ትምህርት ቤቶችን በበቂ ግብዓትና የሰው ኃይል ባልተደራጁበት ሁኔታ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ህዝቡን በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የንቅናቄ  ስራዎችን ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 377 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በ131 ትምህርት ቤቶች ላይ የደረጃ ግምገማ ተካሄዶ ከአንድ ትምህርት ቤት በስተቀር ሁሉም ከደረጃ በታች እንደሆኑ መለየታቸውን  አስታውቀዋል።

በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት ትምህርት ቤቶችን በበቂ ግብዓትና መሰረተ ልማት አደራጅቶ  ደረጃቸውን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የንቅናቄ ሰነድ መሰረት በማድረግ ከክልል እስከ ቀበሌ ግብረ ኃይል የማቋቋም ስራ መጀመሩን  አስረድተዋል።    

የክልሉ የወላጆች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አስምሮ ደርበው በበኩላቸው፤ ለትምህርት ጥራት መሻሻል የወላጆች ፣ የትምህርት ቤቶችና የዘርፉ አመራሮች ቅንጅታዊ አሰራር ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

በተለይም የወላጆች ግንዛቤ ማሳደግ ከተቻለ ለልጆቻቸው ትምህርት መሻሻል የሚሰስቱት  ነገር እንደማይኖር ገልጸው፤ በዚህም  የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የክልሉ ወላጆች መምህራን ህብረት አደረጃጀቱን እስከ ወረዳና  ትምህርት ቤቶች ድረስ  በማጠናከር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል   የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ  ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም