በቆላማ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን ዝናብ በመያዝ ለመኖ ልማት ማዋል ይገባል - ምሁራን

153

ዲላ ግንቦት 26/2015  (ኢዜአ) በቆላማ አካባቢዎች የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ የዝናብ ውሃን በተለያዩ አማራጮች በመያዝ በመኖ ልማቱ ላይ በስፋት መሰማራት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ በተያዘው ዓመት 138 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን መሬት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በመኖ ልማት መሸፈኑም ተገልጿል።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ "አርብቶ አደርና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖ" በሚል ያዘጋጀው አውድ ጥናት ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት መኖና ስነ ምግብ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አዱኛ ቶሌራ እንዳሉት፣ በምስራቅ አፍሪካ ለተራዘሙ ወቅቶች የተከሰተው ድርቅ የአርብቶ አደሩን የመቋቋም አቅም ፈትኖታል።

ከድርቁ በተጨማሪ በዝናብ ወቅቶች ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ታሳቢ ያላደረገ የመኖ አያያዝ ስርአት  አቅምን በማዳከም ጉዳቱን ማባባሱን ጠቅሰዋል።

"በእዚህም በእንስሳቱና በአርብቶ አደሩ ሕይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት ባለፈ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል" ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አዱኛ ገለጻ በቀጣይ ችግሩ እንዳይከሰት አሁን ያለውን መልካም የሚባል የዝናብ ስርጭት በመጠቀም የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

የአርብቶ አደሩን የግጦች መሬት አማራጭ በማያሳጣ መልኩ በቅይጥ ግብርና እንዲሰማራ የሚደረገውን ጥረትንም ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በተለይ እየጣለ ያለውን ዝናብ ያለብክነት በመያዝና የተለያዩ የውሃ አመራጮችን በመጠቀም የመኖ ልማትን በስፋት ማከናወን እንደሚገባ ነው የመከሩት።

ለዚህም ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት በተጨማሪ የምርምር ተቋማት የተቀናጀ የመኖ ስርአትን በመዘርጋት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ፕሮፌሰር አዱኛ አስገንዝበዋል።

የእንስሳት ልማት ለአርብቶ አደሩ ሕይወቱ ቢሆንም የድርቅ ተጋላጭነት ተጠባቂ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ትንሳኤ ታምራት ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የድርቅ ጉዳትን ለመቀነስ ዕቅድን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ከምርምር ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።

ዩኒቨርሲቲው ለተጎጂዎች ፈጣን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ላለፉት ዓመታት በምርታማነት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን የማላማድ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

አውደ ጥናቱ እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማጠናከር ባለፈ የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ የተሻለ ምላሽ ለመስጠት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሰለሞን ዋጋሪ በበኩላቸው ቆላማ አካባቢዎች ለድርቅ ተጋላጭ ቢሆኑም ትልቅ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቀሰዋል።

በአካባቢዎቹ የአደጋ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባለፈ በእንስሳትና እርሻ ልማት የሀገር ኢኮኖሚን ለመደገፍ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአርብቶ አደሩን ባህላዊ እሴት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ውሃ በመያዝ የመኖ ልማቱን በስፋት ከማከናወን ባለፈ አርብቶ አደሩ በእርሻ ልማት እንዲሰማራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ በተያዘው ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት 24 የእንስሳት መኖ ማከማቻና ገበያ ማዕከላት ግንባታ መከናወኑን ነው የገለጹት።

ከእዚህ በተጨማሪ በ138 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የመኖ ልማት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ቀናት በተካሄደው አውደ ጥናት የዘርፉ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን 40 የሚጠጉ ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም