ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ 

228

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) ፦ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ በሚከሰት መፈናቀል በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ። 

በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ግብዓት ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እናቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ረቂቁ አዋጁ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በሚከሰት መፈናቀል ዜጎች የሚያስተናግዱትን ጫና ለመቀነስና ሕጋዊ በሆነ አግባብ ለመምራት ያስችላል ብለዋል። 

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም እንዲሁ።

ረቂቁ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለአገር ውስጥ ለተፈናቃይ ዜጎች ተገቢው ሰብዓዊ የመብት ጥበቃና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል። 

በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቢ ሕግና የረቂቅ አዋጁ አርቃቂ ቡድን አባል ጠገነኝ ትርፌ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ኅብረት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ የካምፓላ ሥምምነት ለረቂቅ አዋጁ መነሻ መሆኑን ገልጸዋል።  

መደረኩም ለረቂቁ ማጠናከሪያ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሚረዳ ጠቅሰው አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ተፈናቃይ ዜጎችን ችግር በማቃለል አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።  

የምክክር መድረኩ ተሳታፊና የሕግ ባለሙያው ሰለሞን ወልደ-ገብርኤል፤ ለተፈናቃይ ዜጎች ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለአስተያየት መቅረቡ መልካም ጅምር መሆኑን ተናግረዋል። 

ዓለም አቀፍ ሕግ መፈናቀልን መከላከል፣ ጥበቃ ማድረግ ወደ ቦታ መመለስን እንደሚደነግግ ጠቅሰው፤ ለተፈናቃይ ወገኖችም ተገቢ ክብር በመስጠት ዘላቂ መፍጥሄ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። 

የዋቻሞ የኒቨርሲቲ ፍልሰት ተመራማሪና ሌላኛው የምክክር መድረኩ ተሳታፊ ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ፤ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የህግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ከቀያቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች ተገቢው ድጋፍና ጥበቃ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በሚከሰት ፍልሰት የተፈናቀሉ ወገኖች በተቋማዊ አሰራር ለማገዝ ይረዳል ብለዋል።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ብሔራዊ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችንና እንደአግባብነቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲካተቱ የሚደረጉ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

በመድረኩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም