በሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘ  ነው- የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት

248

ሀዋሳ ግንቦት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡-  በሀገሪቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን   የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ  በተደረገው  ጥረት  ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘ  መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር የዘርፉ  አመራሮችና  ባለሙያዎች ጋር በሀዋሳ ከተማ  እየተወያየ ይገኛል።
 

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር  አለባቸው ንጉሴ፤ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት የአምራች  ኢንዱስትሪዎች  ልማት   የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው።

በዚህ ረገድ በሀገሪቱ ላሉ አነስኛ፣መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች  በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገላቸው ድጋፍ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የማምረት አቅማቸውን  ከ48 በመቶ  ወደ 53 ነጥብ 5 በመቶ በማሳደግ  ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለው በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን  በማወያየት   ከፍተኛ ስራ በመስራቱ ነው ብለዋል።

በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና ወደ ውጭ የሚላኩትንም ምርቶች በማሳደግ ለዜጎች በርካታ የስራ እድል እንዲፈጠር መደረጉን አመላክተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ዙርያም ቀደም ብሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር ያስፈለገው በዘመኑ የተሻለ  ስራ ለመስራት እንዲቻል ልምዶችን ለመለዋወጥና በእቅድ ላይ መግባባት ፈጥረን ወደ ስራ ለመግባት ነው ብለዋል።

በተለይ አምራች ኢንተርፕራይዞች በፋይናስ አቅርቦት በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅርበት እየሠራን ነው  ነው ያሉት  ዶክተር አለባቸው።  

ዘርፉን በተሻለ  አግባብ ለመምራት  ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መጠናቀቁንና  በቀጣዩ በጀት ዓመት በሙከራ  ደረጃ  ተግባራዊ  እንደሚደረግ አብራርተዋል።
 

በኢንዲስትሪ ሚኒስቴር የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሼቱ ስጦታው በበኩላቸው፤ የውይይት መድረኩ ዓላማ የአምራች ኢንተርፕራይዝ ልማትን የማስፋፋት ተልዕኮን በከፍተኛ ኃላፊነትና በጋራ መወጣት እንዲቻል አንድ እቅድ- አንድ ሪፖርት በጋራ ለማዘጋጀትና በሚኒስቴሩ የተቀመጡ  ዋና ዋና ተግባራት ላይ ለመግባባት መሆኑን ገልጸዋል።

እቅዱ በዋናነት  ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የግብአት አቅርቦት፣የሰው ሃይል ማመቻቸት፣በዘርፉ ጥናትና ምርምር ማካሄድንና አዳዲስ ኢንቨስትመንትን ከውጭ መሳብን እንደሚያካትት አስረድተዋል።

አሁን ላይ ግልጽ የሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ መገባቱ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ  መፍጠሩንም  ተናግረዋል።
 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዘዲን ሙስበሀ፤  በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በዋናነት የሚጠበቀው የስራ እድል መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ እንደ ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ይህ ዘርፍ ለ64 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃርም 98 ሚሊዮን ዶላር ከዘርፉ ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፤ በተለይ በመዲናዋ የሚገኙ 1 ሺህ 965 አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 745 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን አውስተዋል።
 

የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የአምራች ዘርፉ በየደረጃው ለማጠናከር በተደረገው ጥረት በተተኪ ምርቶች የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በዘርፍ 19 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ  ወራት በተለያዩ  ኢንዱስትሪዎች ውሰጥ ለ14 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ማመቻቸት መቻሉን  አስረደተዋል።

ወደ ውጭ የሚላኩ  እንደ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ እሴት የተጨመረበት ቡና፣የአቮካዳ ዘይትና ሌሎችንም አግሮ ፕሮሰሲንግ የኢንዱስትሪ ምርቶችን  ወደ ውጭ በመላክ 77 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ከታቀደው ውስጥ  80 በመቶ  ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም