በሀዋሳ ከተማ በ250 ሚሊዮን ዶላር የሕክምና ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

212

ሐዋሳ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)  ሻሎም ሄልዝ ኬር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በሀዋሳ ከተማ በ250 ሚሊዮን ዶላር ለሚያስገነባው የሕክምና ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ዛሬ ለፋብሪካው የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ እንደገለጹት፣ ፋብሪካው በሕክምና ዘርፍ ያለውን የግብዓት አቅርቦት ችግር ይፈታል።


 

አብዛኞቹ የሕክምና መሳሪያዎችና ግብአቶች በከፍተኛ ዋጋ ከውጭ ሃገር ስለሚገቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

ሻሎም ሄልዝ ኬር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሕክምና ቁሳቀስ ማምረቻ ፋብሪካ በሀዋሳ ከተማ መገንባቱ ችግሩን ለማቃለል ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለኩባንያው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፋብሪካው ተገንብቶ ወደ ማምረት ሲገባ እንደ ሃገር በህክምና ዘርፍ የሚታየውን የግብዓት አቅርቦትን ችግር ከመፍታት ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካም ምርቱን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ያስገኛል ብለዋል።

የፋብሪካው መከፈት የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና በዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ደስታ አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግስት ለፋብሪካው ግንባታ የሚያስፈልገውን መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስረከቡን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ፋብሪካው በተቀመጠለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅም አስገንዝበዋል።

የሻሎም ሄልዝ ኬር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሕክምና መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ መስራችና ፕሬዚዳንት ዶክተር ዊንታ መሃሪ በበኩላቸው፣ ኩባንያው በአሜሪካና ካናዳ እንደሚሰራና ባለፈው ዓመትም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

በሃዋሳ ከተማ ለሚያስገነባው የሕክምና መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ 250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

የፋብሪካው ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ "ፋብሪካው ስሪንጅ፣ መርፌ፣ አይቪ ባግና ማስክን ጨምሮ ስድስት የተለያዩ የሕክምና ቁሶችን" ያመርታል ብለዋል።

የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር ገልጸው፣ ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ ለ5 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ፋብሪካው የተለያዩ የግንባታ ምዕራፎች እንዳሉት ዶክተር ዊንታ ጠቅሰው፣ "በየምዕራፉም ወደስራ ይገባል" ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው ለሀገር፣ ለክልሉና ለከተማ አስተዳደሩ ሰፊ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለውጤታማነቱ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።


 

በሀዋሳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አካባቢ በተዘጋጀ 10 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው ለእዚህ ፋብሪካ በርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና በዶክተር ዊንታ መሃሪ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

 

 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም