ቻይናና ኢትዮጵያ ያሏቸው የባህልና የቋንቋ ልውውጥ ለአገራቱ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ  አለው - በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን

309

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፦ ቻይናና ኢትዮጵያ ያሏቸው የባህልና የቋንቋ ልውውጥ ለአገራቱ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን ገለጹ።

በቻይና መንግሥት አመቻቺነት በኢትዮጵያ የቻይና ቋንቋን በዩንቨርሲቲ ደረጃ ከሚያጠኑ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ቻይንኛን አንድ ክፍለ ጊዜ በሚወስዱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ዛሬ በቻይንኛ የተለያዩ የመድረክ ሥራዎችን አቅርበዋል።
 

በመድረኩ ተማሪዎቹ በቻይንኛ ቋንቋ ንግግሮች፣ የቻይንኛ ሙዚቃና ስፖርት እንዲሁም ልዩ ልዩ ትዕይንቶችን በውድድር አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ  የትብብር መስኮች ያሏቸው ግንኙነት እየተጠናከረ ነው።

ቻይናና ኢትዮጵያ ያሏቸው የባህልና የቋንቋ ልውውጥ ለአገራቱ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው አምባሳደሩ የገለጹት።  
 

በመድረኩ በትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሺፕ ዴስክ የተወከሉት ተረፈ በላይ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የረዥም ዓመታት ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

አገራቱ ያላቸው አጋርነት በተለይም በኢኮኖሚ መስክ ወደ ላቀ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል የባህል ትስስሩ መጠናከሩ ደግሞ የአገራቱን ሁለንተናዊ አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ነው ያስረዱት።  

በተለይም ደግሞ በአገራቱ መካከል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርና ኢኮኖሚያዊ አጋርነቱን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰው አብራርተዋል።  
 

በመድረኩ ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ተማሪዎች በበኩላቸው አንዲህ ያለው ተሞክሮ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳል ነው ያሉት። 

ቢሾፍቱ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምርት ቤት ተማሪ የሆነችው ሲያኔ ታደሰ መርሃ ግብሩ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እድል እንደሚሰጥ ጠቁማለች። 

በተለይም ቻይና አሁን ላይ የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆኗን ገልጻ በመሆኑም የቻይና ቋንቋ ማወቅ በዘርፉ ይበልጥ ተባብሮ ለመሥራት እንደሚያግዝ ተናግራለች።

ሌላኛው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ ተማሪ ናፍያድ ንጋቱ ቻይንኛ የሚማሩ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው እንዲሁም አማርኛ የሚማሩ ቻይናውያን መኖራቸው ትስስሩን ያጠናክራል ብሏል።  

በሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነቱን ለማጠናከር የባህል ግንኙነቱ ትልቅ ጥቅም አለው ያለው ደግሞ በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ ተማሪ በረከት ደመላሽ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም