ጋምቤላ ክልልንና አንፊሎ- ደንቢደሎን የሚያገናኘው መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ጋምቤላ ክልልንና አንፊሎ- ደንቢደሎን የሚያገናኘው መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ተደረገ

ጋምቤላ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) በጸጥታና ብልሽት ምክንያት ለሶስት ዓመት ተቋርጦ የቆየው የጋምቤላ ክልልንና አንፊሎ- ደንቢደሎን የሚያገናኘው መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ተደረገ።
መንገዱ የተከፈተው በአካባቢው ህዝብና በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተቀናጀ ጥረት እንደሆነም ዛሬ በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የአንፊሎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነጋሽ ቀና የመንገዱን መከፈት አስመልክተው እንደገለጹት፤ ወረዳውንና ክልሉን የሚያገናኘው መንገድ በጸጥታና ብልሽት ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት ተቋርጦ በመቆየቱ በሁለቱ ህዝቦች ሁለንተናዊ ግንኙነት ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል።
የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ አበበ በአሁኑ ወቅት መንገዱ በመከፈቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተጀመረው የሰላምና የልማት ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ 104ኛ ራስ ዳሸን ኮር የ35 ዋሊያ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደሳለኝ ሙላው፤ ክፍለ ጦሩ በጋምቤላና በቄለም ወለጋ ተዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሰላም የማስጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ላለፉት ሶስት ዓመታት በጸጥታና በብልሽት ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የጋምቤላ ክልልንና የአንፊሎ ወረዳን የሚገናኘው መንገድ በሰራዊቱና በህዝቡ ጉልበት መጠነኛ ጥገና ተደርጎለት እንዲከፋት መደረጉን አስታውቀዋል።
ሰራዊቱ በቀጣይም የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ በማስጠበቅ የሁለቱ ህዝቦች ያለምንም ስጋት በሰላም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን እንዲያከናውኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።