ተማሪዎችና መምህራን የተሳተፉበት ክልል አቀፍ  የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕይ በባህርዳር ተከፈተ

274

ባህርዳር ግንቦት 26 /2015 (ኢዜአ)፡- በባህርዳር ከተማ  ተማሪዎችና መምህራን የተሳተፉበት ክልል አቀፍ  የሳይንስ ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፈተ። 

በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት የፈጠራ ስራዎች ተወዳድረው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለሚወጡ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተመልክቷል።

 አውደ ርዕዩ  ለ4 ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።

ተወዳዳሪዎቹ  ከሁሉም የክልሉ ዞኖች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 142 ተማሪዎችና መምህራን ይዘው የቀረቡትን የፈጠራ ስራ በ5 ቡድን ተከፍለው መሆኑ ተገልጿል።
 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ  እንዳመለከቱት፤  ከድህነት ለመውጣት የሚያግዙ   የፈጠራ ባለራዕይ ተማሪዎችንና መምህራንን ለማበረታታት በትኩረት ይሰራል።

 የፈጠራ አውደ ርዕዩን በመጎብኘት የፈጠራ ባለቤቶችን ማበረታታት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል። 

ቢሮውም የፈጠራ ባለራዕዮችን በመደገፍና በማበረታታት በአውደ ርዕዩ ተወዳድረው አሸናፊ ለሚሆኑ ተማሪዎችና መምህራን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን ወክለው እንደሚሳተፉ  ጠቁመዋል።

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነር ዶክተር ሳሌ አያሌው በበኩላቸው፤ ተማሪዎችና መምህራን ለውድድር ይዘዋቸው የቀረቡት የፈጠራ ስራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ፈጠራቸውን በአዕምራዊ ንብረት እንዲመዘገቡ  ኮሚሽኑ እገዛ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ሳሌ፤ ውጤታማ የሆኑትን የድካማቸውን ፍሬ እንዲያገኙ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
 

ነዳጅ አልባ ባጃጅ በፀሓይ ሃይል /ሶላር/ የሚሰራና ከወዳደቁ ብረቶች ሰርቶ በአውደ ርዕዩ ለውድድር ይዞ መቅረቡን  የተናገረው  ከምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የበረንታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ጌታቸው አባተ ነው።

ሁለት ሰው እንድትይዝ አድርጎ በሰራት ባጃጅም ዘወትር ከቤቱ ወደ ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ ለትራንስፖርት እየተገለገለባት መሆኑን አስረድቷል።

በቀጣይ አጋዥ አካል ባገኝ የትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለልና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል በብዛት አምርቼ ወደ ገበያ በማቅረብ ራሴንና ሀገሬን ለመጥቀም ራዕይ አለኝ ብሏል። 

ከአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ የስጋዲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የፊዚክስ መምህር መለሰ ግርማ በበኩላቸው፤ በአውደ ርዕዩ ለውድድር ይዞው የቀረቡት ዘመናዊ የእህል ማበጠሪያ ማሽን መሆኑን ገልጸዋል።

"ሳድግ እናቴ ጤፍ ለማበጠር ሁልጊዜ ስትቸገር አይ ስለነበር ይህንን ሊያቃልል የሚችል ዘመናዊ የእህል ማበጠሪያ ማሽን ለመስራት አነሳስቶኛል " ብለዋል።

በውድድሩም ከየምድቡ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለሚወጡ  የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም