ሰራዊቱ ብቃቱን የሚያሳድግበት ምቹ አካባቢ በመፍጠር የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ በቀለ

232

ባህር ዳር ግንቦት 26/2015((ኢዜአ) :-  የአገር መከላከያ ሰራዊት ብቃቱን የሚያሳድግበትና ዝግጁነቱን የሚያጠናክርበት ምቹ አካባቢ በመፍጠር የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ በቀለ ገለጹ። 

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ በሰሜን ምዕራብ ዕዝ መቀመጫ ያከናወነውን የጥገና እና ግንባታ ስራ አጠናቆ ዛሬ ለዕዙ አስረክቧል። 


 

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ በቀለ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት አገርን የመጠበቅ ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው።

አገርን ከማንኛውም ችግር ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ለማድረግም ለሰራዊቱ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያና የመዘጋጃ ካምፕ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰራዊቱ በሰላም ጊዜ ተረጋግቶ የሚኖርበት፣ በስልጠናዎች ብቃቱን የሚያሳድግበትና ለተልዕኮ ዝግጁነቱን የሚያጠናክርበት ምቹ አካባቢ በመፍጠር የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ የዕዙ መቀመጫ የሆነውን መኮድ ካምፕ በማደስና የአጥር ግንባታ ሥራ በማከናወን ምቹ መኖሪያና የስራ ቦታ በማስረከቡ ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው መምሪያው የሰራዊቱንና የአመራሩን የመፈጸም ብቃት የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በዚህም የሬጅመንት፣ የክፍለ ጦር፣ የኮር እና የዕዝ ቢሮዎች፣ መኖሪያዎችንና ሌሎች መጠለያ ካምፖችን በመገንባት መንግስት የሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ መምሪያው 48 የውሃ ጉድጓዶችን በአገር ደረጃ በማስቆፈር ሰራዊቱ የሚገለገልባቸው ሆስፒታሎች፣ ካምፖችና መኖሪያ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ሌተናል ጄኔራል ደስታ የተናገሩት።

በመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ የኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀኔራል ያደታ አመንቴ በበኩላቸው፣ ከመኮድ ካምፕ እድሳት ስራ በተጨማሪ የአጥር ግንባታ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።    


 

የቢሮ ሕንጻ፣ የሎጅስቲክስ ክፍሎች፣ መዝናኛዎች እንዲሁም ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ አዳራሾችና የሰራዊት መኖሪያ ቤቶች ሙሉ እድሳት እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ መኖሪያ እና የመኮድ ካምፕ ጥገናና 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአጥር ግንባታ ስራ በ15 ወራት ጊዜ ውስጥ መከናወኑን በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም