በዞኑ በመኸር ወቅት ከ607 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመኸር ወቅት ከ607 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባህር ዳር ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)--በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በመጪው መኸር ከ607 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት የእርሻ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል ለኢዜአ እንደገለጹት ምርታማነትን ለማሳዳግ አርሶ አደሩ ማሳውን ደጋግሞ በማረስ ለዘር እንዲያዘጋጅ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዞኑ በመጪው የመኸር እርሻ 607ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱንና ከእዚህ ውስጥም ከ500 ሺህ በላይ የሚሆነው መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በትራክተር መታረሱን የጠቆሙት ሃላፊው፣ በእርሻ ዝግጅቱ ከ360 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
አቶ ፈንታሁን እንዳሉት፣ ለዘር የተዘጋጀው መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ15 በመቶ በላይ ብልጫ አለው።
ማሳን ቀድሞ ማዘጋጀት ለምርታማነት ያለውን ፋይዳ አርሶ አደሩ እየተገነዘበ መምጣቱ ለብልጫው ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ታርሶ ለዘር ከተዘጋጀው መሬት ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ቀድመው በሚዘሩ እንደ ማሽላ፣ በቆሎና ሌሎች የሰብል አይነቶች መሸፈኑንም ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
ከልማቱ ተሳታፊዎቹ መካከል በጎዛምን ወረዳ የዳሊጋው ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ይርጋ ሙሉዬ ለመጪው የመኸር እርሻ ከሁለት ሄክታር በላይ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ማሳን ደጋግሞ ማረስ ምርታማነትን ከማሳደግ በላይ አረምን እንደሚያጠፋ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክር መሰረት ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ለዘር ሥራ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ማሳቸውን አርሰው በማለስለስ ግማሽ ሄክታር በሚሆነው ላይ በቆሎ መዝራታቸውን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ አዋበል ወረዳ የከይት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሃብታሙ ሉሌ ናቸው።
መሬቱን ቀደም ብለው ማረሳቸው የዘር ወቅትን ጠብቀው ለማረስ እንዳስቻላቸው የጠቆሙት አርሶ አደሩ፣ የእርሻ መሬትን ደጋግሞ ማረስ ያለውን ጥቅም ካለፉት ዓመታት የራሳቸው ተሞክሮ ማወቃቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በመጪው የመኽር እርሻ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ከ21 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያሳያል።