ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ህዝቡን በማሳተፍ እየተሰራ ነው

ጋምቤላ ግንቦት 26/2015(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ስጋቶችን በመከላከል ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ህዝብን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ለኢዜአ እንደገለጹት በህዝብ ተሳትፎ የጸጥታ ችግሩንና የሙርሌ ታጣቂዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥቃት በመከላከል የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው።

በክልሉ በቅርቡ በኢታንግ ልዩ ወረዳና በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በህዝብና በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በቁጥጥር ስር በማዋል ህዝቡ ወደ ቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ ኡቶው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢታንግ ልዩ ወረዳና በጋምቤላ ከተማ የፌዴራል የጸጥታ አካላት ተሰማርተው የተጠናከረ የጸጥታ ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ ህዝቡ በሰላም እየተንቀሳቀሰ ነው።

ተከስተው የነበሩ መጠነኛ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን የማወያየት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ በማህበራዊ ሚዲያ የክልሉን ጸጥታ ለማወክ እየጣሩ ያሉ አካላትን የመመከት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወደ ክልሉ የኑዌርና የአኝዋሃ ዞኖች ለዘረፋ ሰርጎ በመግባት በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ እየሞከሩ ያሉትን የሙርሌ ታጣቂዎች ለመከላከልም በስጋት ቀጠናዎች የሚሊሻ፣ የፖሊስና የፌዴራል የጸጥታ አካላት እንዲሰማሩ መደረጉን አቶ ኡቶው ገልጸዋል። 

በጋምቤላ ከተማ የሚስተዋለውን የዘረፋና የስርቆት ወንጀል ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ችግር ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አቶ ኡቶው ገልጸው፣ እስካሁን ባለው ሂደት 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኡቶው ገለጻ በከተማው ለዘረፋና ስርቆት ወንጀል መስፋፋት አስተዋጾ ይኖራቸዋል የተባሉትን ባለሁለት እግር የሞተር ተሽከርካሪዎች ማታ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ በጊዜያዊነት እገዳ ተጥሏል።

"የክልሉ ሰላም በጸጥታ አካላት ብቻ ሊረጋገጥ አይችልም" ያሉት ኃላፊው ህዝቡ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም የጀመረውን ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።

ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ፓስተር ኡቦንግ ኡሉም  እና ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ኮንግ ጋድቤል  በሰጡት አስተያየት ከሳምንት በፊት በኢታንግ ልዩ ወረዳና በጋምቤላ ከተማ መጠነኛ የጸጥታ መደፍረስ ተከሰቶ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

ይሁን እንጂ መንግስት ባደረገው ጥረት ችግሩ በቁጥጥር ስር ውሎ ህዝቡ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴው መመለሱን ጠቁመው፣ መንግስት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የጀመራቸው ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ለአብሮነት መስራት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም