አቶ ሰለሞን ሶካ በሞሮኮ በተዘጋጀው በጂኣይቴክስ አውደ ርዕይ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙ ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን ጎበኙ

363

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፡-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በሞሮኮ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ('ጂ ኣይ ቴክስ')  ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙ ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን ጎብኝተዋል።

በሞሮኮ ማራካሽ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደዉ ኮንፍረንስ ላይ የአቅም ግንባታ ስራ ለሙያዊ ልህቀትና ኢኮኖሚ ልማት በሚል በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተካፈሉት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን መጎብኘታቸው ተገልጿል።

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው እና ትኩረቱን በሳይበር ደህንነት፣ በክላውድ ኮምፒውቲንግ ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በፊንቴክ (fintech)፣ በዲጂታል ከተማ፣ አግሪ ቴክ (agritech) መሰል የቴክኖሎጂ ዘርፎች ባደረገው ኮንፍረንስ ላይ ኢትዮጵያ ምርትና አገልግሎቶቿን አስተዋውቃለች።

በጉብኝቱ ወቅት በሳይበርና መሰል ጉዳዮች ላይ አቅም ያላቸው አካላት ከኢመደአ ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባና ተቋሙ ለዚህ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶክተር) ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም