መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ብሩህ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

317

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፦ “መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ብሩህ ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የሁለቱን አገራት ትብብር ሁሉን አቀፍ እና ስትራቴጂካዊ ነውም ብለዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን በቅርቡ በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጉ ይታወቃል።

አቶ ደመቀ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ከቻይናው ሲ ጂ ቲ ኤን 'ሃይ ቶክ' ከተሰኘው ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም  የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ትብብር ጠንካራ እና ወዳጅነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ሁለቱ አገራት ያልተነኩ እድሎችን ለመጠቀም ያላቸው ፍላጎት የወደፊቱን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ብሩህ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። 

የአገራቱ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ፣ ስትራቴጂካዊ እና የጋራ ትብብር ያለው መሆኑ ቻይና ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትልሞች ድጋፍ ለማድረግ ጥሩ መሰረት እንደጣለ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ከሁለትዮሽ ትብብራቸው ባለፈ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ የሚያተኩረው የደቡብ-ደቡብ ትብብር ጽንሰ ሀሳብ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ደመቀ ይህም ለተቀረው የአፍሪካ አህጉር የልማት ሕልሞች ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እና የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም(ፎካክ) በአፍሪካ እና ቻይና ትብብር አፍሪካውያን ሰላማዊ እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድርግ ሕልማቸውን እንዲያሳኩ የሚያግዙ ማዕቀፎች መሆናቸውን ነው አቶ ደመቀ ያስረዱት።    

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት እና የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ሹ ቢንግ የሰላም ጥረቶች ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሰላም ሂደቱን ለማጽናት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጸው በሰላም ሂደቱ የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሚና እንደምታደንቅ ገልጸዋል።

ሌሎችም በአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ በመመራት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ አቶ ደመቀ ጥሪ ማቅረባቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ከትናንት በስቲያ በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መስክ በተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያና የቻይና ወዳጅነትና ትብብርን ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በቆይታቸውም ከቻይና መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ውይይቶቹ የሁለቱን አገራት ግንኙነትና ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር እድል የፈጠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

አቶ ደመቀ በቻይና ባደረጉት ጉብኝት ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ፣ከቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ሃን ዤንግ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን ግንኙነታቸውን ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቤጂንግ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው መክፈታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም