ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ902 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ ለችግኝ መትከያ ዝግጁ ተደርጓል - የኢትዮጵያ ደን ልማት

222

 

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፡- ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ902 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ ለችግኝ መትከያ ዝግጁ መደረጉን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት ከአራት ዓመት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡

የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የደን ሽፋኑን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ታላሚ ባደረገው በዚህ መርሐ ግብር ከተተከለው አጠቃላይ ችግኝ 55 በመቶ የሚሆነው ለጥምር ደን መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተከናወነው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉ በስኬቱና ህዝባዊ ተሳትፎን በማረጋገጥ የሚጠቀስ ፕሮጀክት ነው፡፡  

"በኢትዮጵያ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ካልተተከሉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለከፋ አደጋ የምንጋለጥበት ዘመን በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ችግኝ መትከል የምርጫ ጉዳይ አይደለም" ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
 

በኢትዮጵያ ተራራማ አካባቢዎች እየተራቆቱ፤ አፈር እየተሸረሸረ፤ የውኃማ አካላት እየደረቁ፤ መምጣታቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመው፤ አረንጓዴ አሻራ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ቢያዝም እስካሁን ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። 

ለዚህ ደግሞ ምን አይነት ችግኞች በምን አይነት ሥነ ምህዳርና በምን አይነት አፈር ላይ ይተከሉ የሚለው በጥናት ተለይቶ ለተከላ ዝግጅት መደረጉን በማብራራት፡፡

በዚሁ መሰረት እስካሁን ከ902 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተለይቶ ለችግኝ መትከያ የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 522 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ለደን መለየቱን ጠቁመዋል፡፡

ለችግኝ መትከያ ከተለየው መሬት ውስጥ 257 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ካርታ እንደተዘጋጀለት ነው የገለጹት፡፡
 

በመጀመሪያው ምዕራፍ በተካሄዱት አራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ከዘር መረጣ ጀምሮ በችግኝ ተከላና በእንክብካቤ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አረጋግጠናል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል በሆነው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የዜጎች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ 

ችግኝ መትከል የመርሐ ግብሩ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤የተተከሉ ችግኞች ለሚፈለገው አላማ ውለው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ  የመጨረሻ ግቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮው መርሐ ግብር እስካሁን ወደ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚጠጋ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ሞቶማ ገለጻ፤ በ2015 የበልግ ወቅት በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ድሬዳዋ ከ 250 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች በደን ልማት፣ በምግብ ዋስትና፣ በአፈር ለምነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያመጡትን አዎንታዊ ለውጥ አጥንቶ ይፋ የሚያደርግ ድርጅት መለየቱን ጠቁመዋል።

 

 

 

 

  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም